በ2019 የትምህርት ዘመን 9 የፌዴራል ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በ2019 የትምህርት ዘመን 9 የፌዴራል ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር ዝግጅታቸውን አጠናቅቀዋል አለ ትምህርት ሚኒስቴር፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ክንደያ ገብረሕይወት (ፕ/ር) በሰጡት መግለጫ በ2019 የትምህርት ዘመን አዲስ ትምህርት የሚጀምርባቸውን ትምህርት ቤቶች ጨምሮ በ9 የፌዴራል ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የሚተዳደሩት እነዚህ ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቃት ያላቸው፣ ተወዳዳሪ የሆኑ፣ ሥነ ምግባርን የተላበሱ እንዲሁም ለሀገር የሚበቁ የወደፊት መሪዎችን ለማፍራት የሚያግዙ ተቋማት መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ከመደበኛ ትምህርት ቤቶች በተለየ መልኩ በልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶቹ የተግባርና የክህሎት ትምህርት ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥም ተገልጿል።
ይህም ተማሪዎች የተለያዩ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ፣ ቴክኖሎጂን በተግባር እንዲጠቀሙና ለወደፊት የሥራና የትምህርት ዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
ከቻይና መንግሥት ጋር በተደረገው የትብብር ስምምነት መሠረት ከሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ጀምሮ የቻይንኛ ቋንቋ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በመሆኑም ወላጆች፣ መምህራንና የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ተማሪዎች ይህንን እድል እንዲጠቀሙበት የማበረታታትና የማስተባበር ሥራ መስራት እንዳለባቸው ተመላክቷል፡፡
የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ባለፉት 5 ዓመታት በትምህርት ዘርፉ ከተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት ሥራ በጀመሩ 5 የልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ 1ሺህ 250 የተሻለ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች የትምህርት እድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
በ2019 የትምህርት ዘመን አዲስ ትምህርት በሚጀምርባቸውና ባለፈው ዓመት ትምህርት በተጀመሩባቸው ትምህርት ቤቶች የ9ኛ እና 10ኛ ክፍል ተማሪዎች ምዝገባ እየተከናወነ ሲሆን፤ ተማሪዎች ካሉበት ቦታ ሆነው በበይነ መረብ መመዝገብ እንደሚችሉም ነው የተገለጸው፡፡
የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በመላ ሀገሪቱ በስፋት እንዲዳረሱ ትምህርት ሚኒስቴር በሁሉም ክልሎች 13 ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑም ተመላክቷል።