በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የጥጥ ምርትን ለማስፋት በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት መጥቷል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በክልሉ የጥጥ ምርትን ለማስፋት በተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት መጥቷል አለ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ፡፡
የቢሮው ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በደቡብ ኦሞ ዞን በጥጥ ልማት ዘርፍ እየተሰራ ያለው ስራ ከውጭ የሚገባውን የጥጥ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልጸዋል፡፡
ምርቱን በስፋትና በጥራት ለማምረት የግል ባለሀብቱን ያሳተፈ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ጥጥን ጨምሮ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ የግብርና ምርቶችን ለማልማት የሚያስችል አቅም እንዳለ ገልጸዋል፡፡
ልማታዊ ባለሀብቶችን በማበረታታት የሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት መሪ ተዋናይ እንዲሆኑ የክልሉ መንግሥት የማያቋርጥ ድጋፍ እንደሚያደርም አመልክተዋል፡፡
በግሉ ዘርፍ በደቡብ ኦሞ ዞን በባና ፀማይ ወረዳ የወይጦ ወንዝን በመጥለፍ ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ጥጥ እያመረተ ያለ የእርሻ ልማት ድርጅት መኖሩን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሌሎች ባለሃብቶችም የክልሉን እምቅ አቅም በመረዳት ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡