የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል በደብረ ታቦር ከተማ በተለያዩ ሁነቶች ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደብረ ታቦር (ቡሄ) በዓል በደብረታቦር ከተማ በርዕሰ አድባራት ደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን በተለያዩ ሁነቶች ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የከተማዋ ከንቲባ ደሴ መኮንን ቡሄ ብርሃን የተገለጠበት እና መልካም ድርጊት የተፈጸመበት በመሆኑ የአንድነት፣ የደስታና የመተሳሰብ በዓል ነው ብለዋል፡፡
ይህ በዓል ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በደብረታቦር ተራራ የገለጠበት በዓል ሲሆን፤ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋዕዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ነው፡፡
በበዓሉ ላይ ችቦ ይበራል፣ ሙልሙል ይጋገራል፣ ጅራፍ የማጮህ ተግባር የሚካሄድ ሲሆን፤ ሁሉም ነገሮች የራሳቸው ምሳሌ እንዳላቸው ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡
ሙልሙሉ ብርሃነ መለኮት ሲገለጥ እረኞች የመሸ ስላልመሰላቸው በጊዜ ወደ ቤታቸው ባለመመለሳቸው ወላጆቻቸው ስንቅ ይዘውላቸው መሄዳቸውን የሚያሳይ ነው፡፡
ችቦው ደግሞ የብርሃነ መለኮት መገለጥ ምሳሌ ሲሆን፤ የጅራፉ መጮህ በደብረ ታቦር ተራራ ድምጸ መለኮት የመሰማቱ ምሳሌዎች መሆናቸውን የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡
ይህ የክረምት ማብቂያ እና የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ በዓል የእምነቱ ተከታዮች በሆኑ ምዕመናን ዘንድ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡
በዓሉ ከሐይማኖታዊ ሥርዓቱ ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ ስለሚሆን ለኢኮኖሚ መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት መገለጹን ከከተማው ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በዓሉ ከደብረ ታቦር ከተማ በተጨማሪ በተለያዩ ቦታዎች እየተከበረ ይገኛል፡፡