ኢትዮጵያ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ይማቅቁ የነበሩ አፍሪካውያን ነጻ እንዲወጡና ሉዓላዊነታቸውን እዲያገኙ ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ማድረጓ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡
በዚምባብዌ የኢያን ስሚዝን ዘረኛ አገዛዝና እና በደቡብ አፍሪካ ሲካሄድ የነበረውን ጸረ አፓርታይድ ትግል በስልጠና፣ በትጥቅ እና በዲፕሎማሲው መድረክ ያደረገችው ድጋፍ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ለአፍሪካዊያን አርነት መውጣት እንዲሁም የአህጉሪቱን አጀንዳዎች በተለያዩ የዓለም መድረኮች በማቅረብ ለተወጣችው ታሪካዊ ሚና እንዲሁም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ሕብረት እንዲመሰረት ለተጫወተችው ግንባር ቀደም ሚና የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ ለመሆን አስችሏታል፡፡
በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ የአህጉሪቱን አንድነትና ትስስር በግንባር ቀደምትነት ስትሞግትና ስታስከብር የኖረች በመሆኗ፤ በዲፕሎማሲው መድረክ የጎላ ተጽዕኖና የመሪነት ሚና አላት።
የዛሬው የአፍሪካ ሕብረት በጽኑ መሠረት ላይ እንዲመሰረት በማድረግ ረገድ የላቀ የታሪክ አሻራ አኑራለች፡፡
ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ መነሻና ለአህጉራዊ ውህደት የቆመች ፈር ቀዳጅ ሀገር ናት፡፡
በተለይም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ አፍሪካ ሕብረት ሲመሰረት ተፈጥሮ የነበረውን የፖለቲካ ልዩነት በማሸማገል ተጻራሪ የነበሩትን የካዛብላንካ እና የሞንሮቪያ ቡድኖች በማስታረቅና በማቀራረብ ረገድ እጅግ ታላቅ ታሪካዊ ገድል ፈጽማለች፡፡
ከዚህ ታሪካዊ ሚናዋ ባሻገር ሀገሪቱ በሊግ ኦፍ ኔሽን አባልነት በኋላም ድርጅቱ በተባበሩት መንግሥታት ሲተካ መስራች በመሆን የአፍሪካዊያን ድምጽ እና እንደራሴ ሆና ስታገለግል ቆይታለች፣ አሁንም እያገለገለች ትገኛለች፡፡
በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በሺዎች የሚቆጠር ሠራዊቷን በማሰማራት፣ የአህጉሪቱን ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ሁልጊዜም ግንባር ቀደም ተሰላፊ ናት።
በተጨማሪም እንደ ተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) ያሉ ታላላቅ መድረኮችን በማስተናገድ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀረጻና በአየር ንብረት ለውጥ ዲፕሎማሲ የላቀ ድርሻ ትጫወታለች።
አፍሪካ እንደ ብሪክስ (BRICS) እና ቡድን 20 ባሉ ዓለም አቀፍ የፖለሲ እና የኢኮኖሚ ወሳኝ መድረኮች ላይ አንድ ወጥ የሆነ ጠንካራ ድምጽ እንዲኖራት በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ የማይተካ ሚና እየተጫወተች ነው።
ይህ ዘመናትን የተሻገረ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ሚና አህጉሪቱ የሚገጥሟትን ፈተናዎች ተግባራዊ መፍትሔዎች በመስጠት ሂደት ከፍ ያለ ኃላፊነት እንድትሸከም ያደርጋታል፡፡
ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ ዓለም አቀፋዊ የዲፐሎማሲ ልምድና ከምትሸከመው አህጉራዊ ኃላፊነት አኳያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ሁለገብ ትብብር በማጠናከር አስተማማኝ አጋር ሆና ቀጥላለች።
ይህም አፍሪካውያን በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ በአንድነት እንዲቆሙና ድምጻቸውን እንዲያሰሙ በማስቻል ረገድ የኢትዮጵያ የመሪነት ሚና አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በአብረሃም አበራ