ምቹና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ከተማነቷን እያስመሰከረች የምትገኘው አዲስ አበባ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ በኮሪደር ልማት መልሶ ማልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ተሞሽራለች፤ ፍጹም ተቀይራለች ፤ የከተማ ውበት ልክ መሆን ጀምራለች፡፡
መንገዶች ሰፍተዋል ፣ ጨለማ የነበሩ ጐዳናዎቿ በርተዋል፣ የእግረኛ መንገድ ተለይቶ ተገንብቷል፣ ከዚህ በፊት ያልነበሩ የብስክሌት መንገዶች ዛሬ የአዲስ አበባ መገለጫ መሆን ችለዋል።
ትላንት መንገዶች በመኪና ፓርኪንግ ይጨናነቁ ነበር ዛሬ ግን የለም፡፡ በየቦታው የመኪና ፓርኪንግ ቦታዎች ለምተዋል፡፡ የትራፊክ ፍሰቱንም በማሣለጥ የከተማዋ ውበት መጠበቅ ተችሏል፡፡
አዲስ አበባ 2 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው አረንጓዴ ሽፋኗ ወደ 24 በመቶ አድጓል፡፡ ከአፍሪካ አስሩ ፅዱ ከተሞች አንዷ በመሆንም በዓለም አቀፍ ደረጃም እውቅናን አግኝታለች፡፡
አዲስ አበባ ጽዱ፣ ውብ እና መሰረተ ልማቶች የተሟሉላት ከተማ መሆን በመቻሏ በርካታ ኮንፈረንሶች፣ ስብሰባዎችና ጎብኚዎች የማስተናገድ ብቃቷ እያደገ መጥቷል፡፡
በዚህም የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ ይበልጥ ጎልብቶ፣ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካውያን ዋና ከተማችን ብለው የሚጠሯት የጋራ ኩራታችን ሆናለች።
መዲናዋ የነበራት 74 በመቶ የጎስቋላነት ገጽታ ወደ 30 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል፡፡ በከተማችን ምንም እንኳን መሰረታዊ ለውጦች ቢመዘገቡም ዛሬም ብዙ መስራት ይጠበቃል፡፡
ለዚህም በቀጣይ በጀት ዓመት የሚተገበሩ የትኩረት ማዕከል ተብለው የተለዩ ዋና ዋና ተግባራት በዋናነትም ከተማችን አዲስ አበባ ለነዋሪዎች ምቹ እና ዓለም አቀፍ ተወደዳሪ ከተማነቷን የሚያረጋግጡ ናቸው።