የወርቅ ምርት፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት አንዱ ምሰሶ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት በማዕድን ዘርፍ በተለይም በወርቅ ምርት ላይ ያደረገው ማሻሻያ እና የትኩረት አቅጣጫ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ወርቅን ጨምሮ እምቅ የማዕድን ሃብት ያላት ቢሆንም ዘመናዊ የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎች በስፋት ባለመኖራቸው ምክንያት የዘርፉ አስተዋጽኦ ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል።
በመደመር መንግሥት በተከናወኑ ማሻሻያዎች እና የሪፎርም ሥራዎች ዘርፉ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል፡፡
የሪፎርም ሥራዎችን ተከትሎም እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት የሆነችው የኢትዮጵያ ወርቅ ሃብት እድገት ከፍተኛ እመርታ አስመዝግቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ከ1984 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ውስጥ ከወርቅ ወጪ ንግድ ያገኘችው አጠቃላይ ገቢ 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ብቻ እንደነበር መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
በመደመር መንግሥት በተደረጉ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ማሻሻያዎች እና ቁርጠኛ አሰራር በአንድ ዓመት ብቻ ሀገሪቱ 5 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ገቢ ከወርቅ ምርት ማግኘት ችላለች።
በዚህም በአንድ ዓመት የተገኘው የወርቅ ገቢ ከለውጡ በፊት በነበሩ 27 ዓመታት ከተሰበሰበው አጠቃላይ ሃብት በላይ ሆኗል፡፡
ይህ ስኬት የመጣው በሕገ ወጥ መንገድ የሀገር ሀብት ወደ ግል ኪስ እንዳይገባ በመደረጉ እና የወርቅ ሃብትን በአግባቡ መጠቀም በመቻሉ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የወርቅ ጉዞ በጥሬው ማዕድን በመሸጥ ብቻ የሚቆም አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ታሪኳን በመቀየር የመጀመሪያውን ግዙፍ የወርቅ ማጣሪያ ፋብሪካ በመገንባት ላይ ትገኛለች።
ይህ ፋብሪካ ጥሬ ወርቅን ወደ ተጣራ ንጹህ ወርቅ በመለወጥ የሀገሪቱን እሴት ከፍ በማድረግ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን የወርቅ ዋጋ ያሳድጋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው የኩርሙክ ወርቅ ፋብሪካ፣ የቱሉ ካፒ ወርቅ ልማት እና በጋምቤላ ክልል የተጀመሩ ዘመናዊ የማዕድን ፕሮጀክቶች ሀገሪቱን የአፍሪካ የወርቅ ማዕከል እያደረጓት ነው፡፡
በዚህም ወርቅ ለዘመናት የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ቁንጮ የነበረውን ቡናን በመገዳደር የኢኮኖሚ ምሰሶ ሆኗል፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በምታከናውናቸው ተግባራት ከድህነት ሰንሰለት ተላቃ ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
በእውቀት እና በሀገር በቀል እምቅ አቅም እየተገነባ ያለው ስኬት የነገዋን ኢትዮጵያ በጽኑ መሰረት ላይ የሚያቆም ነው፡፡
በእመቤት ሲሳይ