ምክክሩ ለሀገራችን የሚጠቅሙ ሀሳቦች ላይ በጋራ መግባባት ላይ የደረስንበት ነው – ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ)የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎች ምክክሩ ለሀገራችን የሚጠቅሙ ሀሳቦች ላይ በጋራ መግባባት ላይ የደረስንበት ነው አሉ።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው ሃገራዊ የምክክር ጉባኤ ወደ ማጠቃለያው ምዕራፍ እየተቃረበ ይገኛል።
በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ እየተሳተፉ የሚገኙ ወጣት ተመካካሪዎች ምክክሩ የሁሉም ተመካካሪ ድምጽ የተሰማበት እና ኢትዮጵያ የራሷን ችግሮች በራሷ እየፈታች ያለችበት ትልቅ መድረክ ነው ብለዋል።
ከተመካካሪዎቹ መካከል ወጣት ታረቀኝ በላቸው የምክክር ጉባኤው ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር መሆኗን ማሳያ ነው ሲል ተናግሯል።
እንዲሁም ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የተወጣጡ ኢትዮጵያውያን ለጋራ መግባባት በአንድነት የተሰበሰቡበትና የአፍሪካ ሀገራትም ልምድ መቅሰም የሚችሉበት መድረክ መሆኑን አንስቷል።
ሌላኛዋ ተመካካሪ ወጣት ገነት መለሰው የምክክር ሂደቱ አካታች በመሆኑ ሀገራዊ መግባባትን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋገጥ እንደሚሆን ያላትን ተስፋ ገልጻለች።
ምክክሩ ለሀገረ መንግስት ግንባታ በአንድነት የቆምንበት ነው ያለው ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ ወጣት ፍቲ ሀሠን ነው።
ሌላኛዋ ተመካካሪ መድሃኒት ምትኩ በበኩሏ ታሪካዊ እና የመጀመሪያ የሆነው ይህ ምክክር አለመግባባቶችን በምክክር መፍታት እንዳለብን የሚያስገነዝብ መድረክ ነው ማለቷን ኢዜአ ዘግቧል።