Fana: At a Speed of Life!

በማምረት ሀገር ማጽናት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የወደፊቱን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አቅጣጫ ለመቀየር፣ የሀገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማጎልበት፣ የውጭ ምርቶችን ጥገኝነት ለመቀነስና ዘላቂ የኢንዱስትሪ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የታለመ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።

ይህ ግዙፍ ጥረት በቀላሉ ጊዜያዊ ዕድገት ማስመዝገብ ብቻ ሳይሆን፤ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን የማንኛውም ሀገር አቀፍ ችግሮችና ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ጫናዎች የማይበግሩት ጠንካራ መዋቅር ላይ የመገንባት ታላቅ ራዕይ አለው።

በንቅናቄው በተወሰዱ የተቀናጁና መዋቅራዊ የለውጥ እርምጃዎች ምክንያት በኢንዱስትሪው ዘርፍ አበረታችና ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

የኢንዱስትሪዎች አማካይ የማምረት አቅም ቀደም ሲል ከነበረበት የ47 በመቶ ዝቅተኛ ደረጃ ወደ 67 በመቶ ከፍ ብሏል።

በተያያዘም የዘርፉ ዓመታዊ ዕድገት ከ4 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 10 ነጥብ 7 በመቶ በማደጉ ጠቅላላ የምርት መጠኑ 195 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ደርሷል።

325 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በአዲስ መልክ ሥራ የጀመሩ ሲሆን፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ 830 ኢንዱስትሪዎች ወደ ሙሉ ምርት ተመልሰዋል።

በተጨማሪም እስከ 90 ሚሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 13 ሺህ 800 አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች መደበኛ የምርት ሥራቸውን ጀምረዋል።

የሀገር ውስጥ ምርቶች የገበያ ድርሻም ከ30 በመቶ ወደ 41 በመቶ ያደገ ሲሆን፤ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚያሳዩት ለገቢ ምርቶች ይወጣ የነበረ ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተችሏል።

ንቅናቄው ውጤታማ መሆኑን ከሚያሳዩት ዋና ዋና ስኬቶች መካከል የመከላከያና የፖሊስ የደንብ ልብሶች እንዲሁም የቢራ ገብስ ምርት በአሁኑ ወቅት 100 በመቶ በሀገር ውስጥ መመረታቸው ነው።

ለዚህ ታላቅ ስኬት ዋናው የፋይናንስ አቅርቦት ማደጉ ሲሆን፤ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የቀረበው ብድር ከ8 ነጥብ 1 ቢሊየን ወደ 50 ቢሊየን ብር፣ ለከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ከ52 ቢሊየን ወደ 262 ቢሊየን ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል።

በሌላ በኩል የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ውስጥ ከ235 ሺህ በላይ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

በተጨማሪም በ2017 የበጀት ዓመት ተኪ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ብቻ 289 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘት የተቻለበትም ነው።

በዘርፉ የ10 ዓመታት የረጅም ጊዜ ዕቅድ መሠረት የኢንዱስትሪውን ሀገራዊ የምርት ድርሻ ከ6 ነጥብ 9 በመቶ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ፣ የወጪ ንግድ ገቢን ከ400 ሚሊዮን ዶላር ወደ 9 ቢሊየን ዶላር፣ እንዲሁም የማምረት አቅምን ወደ 85 በመቶ ለማድረስና ለ5 ሚሊየን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ እየተሠራ ላለው ስራ ትልቅ መስረት የጣለ ነው።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሀገሪቱ በራሷ ምርትና አቅም የመቆም ህልሟን ወደ እውን የምትቀይርበት፣ የወደፊቱን የ10 ዓመት ስትራቴጂካዊ ግቦች የምታሳካበት እና የኢንዱስትሪ መዋቅሯን በጽኑ መሠረት ላይ የምትገነባበት ወሳኝ ሀገራዊ ምዕራፍ ነው።

በአብረሃም አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.