70 ሺህ 544 ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አምጥተዋል – ትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ 550 ሺህ 210 ተማሪዎች ውስጥ 70 ሺህ 544 ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አምጥተዋል አለ የትምህርት ሚኒስቴር፡፡
የትምህረት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በዘንድሮ ዓመት የተሻሻለ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ዘንድሮ በአጠቃላይ ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ማለፍ የቻሉት 70 ሺህ 544 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ 12 ነጥብ 8 በመቶ የሚሆኑት ተማሪዎች 50 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ማምጣታቸውን አብራርተዋል፡፡
በዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና 563 ሺህ 960 ተማሪዎች ተመዝግበው 550 ሺህ 210 ተማሪዎች ፈተናውን መውሰዳቸውን ጠቁመዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 32 ነጥብ 3 በመቶ ተማሪዎችን በማሳለፍ ቀዳሚ ነው ብለዋል።
በዓመቱ ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል 62 በመቶ የሚሆኑት በኦንላይን መፈተናቸውን አስረድተዋል፡፡
በ2018 የትምህርት ዘመን አጠቃላይ 563 ሺህ 501 ተማሪዎች በ607 የፈተና ማዕከላት ውስጥ የተፈተኑ ሲሆን ፈተናው በ6 ዙሮች መሰጠቱን አስታውሰዋል።
88 ት/ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ያሳለፉ ሲሆን 565 ት/ቤቶች ደግሞ ምንም ተማሪ ማሳለፍ እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡
ካለፉት ተማሪዎች መካከል በተፈጥሮ ሳይንስ 16 ነጥብ 5 በመቶ ሲሆኑ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 8 ነጥብ 33 በመቶ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
በጀማል አህመድ