በስኬት የተጠናቀቀው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የተካሄደው ሀገራዊ የምክክር ሂደት በሀገሪቱ የፖለቲካና ማኅበራዊ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና ለአፍሪካውያን የጽናት ማሳያ የሆነ ታሪካዊ ክስተት ነው፡፡
ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በዛሬው እለት በስኬት ተጠናቅቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ዘላቂ ሰላም፣ እርቅና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያለመ ነው።
ኮሚሽኑ ባካሄዳቸው መድረኮች የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ የሲቪል ማኅበራትን፣ ሴቶችንና ወጣቶችን ያካተተ ሰፊና አካታች ተሳትፎ ያደረገ ሀገራዊ መድረክ ነበር።
ከየወረዳውና ክልሉ የተሰበሰቡት አጀንዳዎች የሕዝቡን እውነተኛ ፍላጎትና ሥጋት በማንጸባረቃቸው ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ሕዝባዊ መሰረት ያለው እንዲሆን አድርጎታል።
በተካሄዱት ተከታታይ ውይይቶች ተሳታፊዎች የቆዩ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን በማመላከታቸው የፖለቲካ ባህልን ከግጭት ወደ ውይይት ለማሸጋገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በተጨማሪም ለአፍሪካውያን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን መርህ በተግባር ያረጋገጠው ይህ ሂደት፣ ኢትዮጵያ ውስብስብ ፈተናዎችን በራሷ ዜጎች ውይይት ለመፍታት ያሳየችውን ጽናት በአህጉር አቀፍ ደረጃ ማሳያ አድርጓታል።
በአጠቃላይ በሂደቱ የተመዘገበው ስኬት በሕዝቦች መካከል እውነተኛ እርቅ ለማውረድ፣ ወንድማማችነትን ለማጠናከር እና ጠንካራና ሰላማዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል አስተማማኝ መሠረት የሚጥል ነው።
በአብረሃም አበራ