ኢትዮጵያ ሁሉንም ፈተና በጥበብና በትዕግሥት በማለፍ አሸንፋለች – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ኢትዮጵያ ሁሉንም ፈተና በጥበብና በትዕግሥት በማለፍ አሸንፋለች አሉ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ በስኬት በመጠናቀቁና ኢትዮጵያ ስላሸነፈች እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል፡፡
ባለፉት 46 ቀናት ከሁሉም አካባቢና የህብረተሰብ ክፍል የተወከሉ 4 ሺህ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን ጠቅሰው፤ ስኬቱን የምንመዝነው በተሻገርናቸው ፈተናዎች፣ በተፈጠረው አዲስ ባህል እና በተግባባንባቸው ምክረ ሀሳቦች ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ምክክሩ ሁሉንም ጥያቄዎች በአንድ ጀንበር አይፈታም። ሁሉንም ቁስሎች አይፈውስም። ለሁሉም ቅሬታዎች ፍጹም መፍትሄ ሊያቀርብ አይችልም ነው ያሉት።
በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት የተፈጠሩ ችግሮችና ያልተመለሱ ጥያቄዎች ለዘመናት በየሥርዓቱ ሲዳፈኑ ኖረዋል፤ በኃይል ፍላጎትን ለማሳካትም ተሞክሯል። ይህ ደግሞ ቁስሎችን አባብሷል፤ ሀገራዊ ዕዳንም ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ማሸጋገሩን አመልክተዋል።
ሀገርን እግር ተወርች አስሮ የቀፈደዳትን ችግር በምክክር ለመፍታት ሲታሰብ ምክክሩ እንዳይጀመር፣ ሲጀመርም እንዳይቀጥል፣ ሲካሄድም እንዳይሳካ ብዙ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ሁሉንም ፈተና በጥበብና በትዕግሥት በማለፍ ኢትዮጵያ አሸንፋለች ሲሉም አብራርተዋል።
ኢትዮጵያውያን በልዩነታቸው ውስጥ መምከር፣ መደማመጥና መግባባት እንደምንችል ከእኛ ብዙ ለሚጠብቁ አፍሪካውያን በእርግጥም አስመስክረናል ነው ያሉት።
በወሳኝ አጀንዳዎች ላይ መግባባት ተፈጥሯል፤ የቀሩ ሌሎች ጥያቄዎች ደግሞ ተጨማሪ ሥራ ይፈልጋሉ። ይህም የጉዞው አካል መሆኑን መረዳት ያሻል ሲሉም ጠቁመዋል።
ለዘመናት ተከድነው የቆዩ፤ ታሽገው የቆሰሉ ብዙ ጉዳዮች ነበሩን፡፡ አየር ሲነካቸው የሚፈጠረው ችግር የሚጠበቅ ነው፡፡ የውይይት ባህል ከመዳከሙ ጋር ተደምሮ እንዲህና እንዲያ መባባሉ አያስገርምም፡፡ ዋናው ወደፊት መጓዛችን ነው፡፡ እየተግባባንና እየተሻገርን መቀጠላችን ነው ብለዋል፡፡
በመመካከራችን ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ዕንቅፋት በነበሩት ብዙ ጉዳዮች ላይ ተግባብተንባቸዋል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ከጫካ ወደ አዳራሽ፣ ከግርግር ወደ ምክክር የተዛወረ አዲስ ባህል መፈጠሩን ገልጸው፤ ነገሮችን በሐሳብ እንጂ በጠመንጃ መፍታት እንደማይቻል፣ እንደማያዋጣም ታይቷል፡፡ ይህ አዲስ ባህል ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም ሲሉም አስረድተዋል፡፡
እያደገና እየተሻሻለ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ልማድና መልክ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ይህ የምክክር ባህል አሁንም ገና ለጋ ነው ብለዋል።
ጥበቃ፣ ልምምድ፣ ትዕግስት እና ድፍረት ይፈልጋል። እንቅፋቶች ይኖራሉ። ያከራከሩ ጉዳዮች ይኖራሉ። መልካም ጅምሮችን መውሰድ እና ይበልጥ ማሻሻል እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
ቅሬታዎቻችን ከጋራ ሀገራችን እንደማይበልጡ መተማመን ይኖርብናል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት 46 ቀናት ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን ከመጎሻሸም ይልቅ አብረን መምከር እንደምንችል አሳይተናል ብለዋል።
ይህ ምክክር እንዲሳካ ላደረጋችሁ ኮሚሽነሮች፣ ተመካካሪዎች፣ አመካካሪዎች፣ ባለሙያዎች፣ ሚዲያዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምስጋና ይገባችኋል፡፡ ታሪክ ምንጊዜም ሲያወሳችሁ ይኖራል ሲሉም ገልጸዋል፡፡