ስለኢትዮጵያ የሚጸልዩት ኡሁሩ ኬንያታ
የኢትዮጵያ ሰላም ጥቅሙ ከኢትዮጵያ ያልፋል። ከቀጣናውም ይገዝፋል።
ኢትዮጵያ የግፉአን ሁሉ የነጻነት ምልክታቸው ናት። በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና መልክዓ ፖለቲካ አውራ ሀገርም ናት። የአፍሪካ መዲና የመቻልም ምልክት ናት።
የምስራቅ አፍሪካ የታሪክና የፖለቲካ እጣፈንታ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ መረጋጋት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው።
የኬንያ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ጉባኤ መዝጊያ ላይ ተገኝተው «ሁልጊዜም ስለ ታላቋ ኢትዮጵያ ሰላም እጸልያለሁ» ሲሉ የተናገሩት ታሪካዊ ቃል፣ የዚሁ እውነታ ግልጽ ማረጋገጫ ነው።
የፕሬዚዳንቱ ንግግር በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የተመዘገበውን ታሪካዊ የሰላም ርምጃ የሚያበስር ከመሆኑም በላይ፣ ኢትዮጵያ ለአህጉረ አፍሪካ ያላትን ተምሳሌታዊነትና አህጉራዊ ሚና ዳግም ያረጋገጠ ነው።
የኡሁሩ ኬንያታ ምስክርነት ኢትዮጵያ በታሪካዊ አጋጣሚዎች ሁሉ የመላው ጥቁር ህዝቦች ተስፋና መሰረታቸው ሆና መዝለቋን ያበስራል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለወረራና ለቅኝ ግዛት ያልተንበረከከች የታሪክ ኩራት መሆኗን ያነሱት ኡሁሩ ኬንያታ፣ በዓድዋ የተቀዳጀችው ድል የጦር ሜዳ ስኬት ብቻ እንዳልሆነ አስምረውበታል።
የዓድዋ ድል የመላው ጥቁር ህዝቦች የነጻነትና የሰብአዊ ክብር ምልክት ሆኖ ያበራ ችቦ ሲሆን፣ ይህ ታላቅ ድል ሊገኝ የቻለውም ኢትዮጵያውያን በኅብረ-ብሔራዊ አንድነታቸውና በጋራ መቆማቸው ነው።
የኢትዮጵያ ታላቅነት መሰረቱ የልዩነቶቿ ውበትና ኅብረብሔራዊነቷ ነው። ኢትዮጵያውያን ጠላት በመጣ ጊዜ ሁሉ ከአለት የደደረ፣ ከብረት የጠነከረ አንድነትን አሳይተዋል።
በሀገሪቱ ውስጥ ማንኛውም ወገን ለብቻው ተነጥሎ ድል ማስመዝገብ እንደማይችል ትናንትናና ዛሬ ያረጋገጡት ሀቅ ነው። ኡሁሩ ኬንያታም ለኢትዮጵያ ጉዳይና ወደፊት ጉዞ ወሳኙ በውጭ አካላት የሚደረግ ጣልቃ ገብነት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያን እና የታሪካቸው ባለቤትነት ብቻ እንደሆነ አስምረዋል።
ኢትዮጵያ ሁሉንም ህዝቦቿን የምትፈልግ እና የትኛውንም ድምጽ ሳታገል የምታቅፍ በመሆኗ፣ ዛሬ በምክክሩ በኩል የሁሉም ወገን ድምጽ የሚሰማበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍታለች።
በዓለም ላይ የሐሳብ ልዩነትና ግጭት የሌለበት ቦታ ወይም ማህበረሰብ የለም። ዋናውና ወሳኙ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በውይይት ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ መፍትሔ የመፈለግ ሰልጣኔ መኖር ነው።
የዓለም አቀፍ የሰላም ጥናቶችና እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ ሀገራት ልምድ እንደሚያሳየው፣ በኃይል የሚደረግ ፍልሚያ አሸናፊና ተሸናፊን በመፍጠር አዲስ የቂም አዙሪት ከመውለድ ባለፈ ዘላቂ ሰላምን አያመጣም። በውይይት ጠረጴዛ ዙሪያ መቀመጥ ግን የሁሉም ወገን ድምጽ እንዲሰማ በማድረግ ዘላቂና ፍትሃዊ መፍትሔን ያስገኛል።
የኡሁሩ ኬንያታ ምስክርነት እንደሚያስረዳው፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር በስኬት መጠናቀቁ ለሀገሪቱ ዘላቂ መግባባት ጠንካራ መሠረት ጥሏል።
ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው የገጠሟቸውን ፈተናዎች በጋራ የመከቱትን ያህል፣ ዛሬም በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው የጀመሩት የምክክር ባህል ለአፍሪካና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ትልቅ የሰላም ትምህርት የሚሰጥ አዲስ የጥበብ መንገድ ነው።