Fana: At a Speed of Life!

የተፈጥሮ እና የታሪክ ሐቅ ፡ የባህር በር 

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር ሕልውና፣ የኢኮኖሚ ጥንካሬና የጂኦፖለቲካዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከሚወሰንባቸው መሠረታዊ ነገሮች መካከል ቀጥተኛ የባህር በር ባለቤትነት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል።

የባህር በር የዓለም ንግድ ስርዓት የሚተነፍስበት፣ አህጉራትንና ሕዝቦችን የሚያገናኝ የኢኮኖሚና የሉዓላዊነት መሰረት ነው።

ለኢትዮጵያ ደግሞ የባህር በር ጉዳይ የታሪክ፣ የተፈጥሮ እና የፍትሐዊነት ጥያቄ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ረጅም ዘመናት የወደቦች ባለቤት የነበረችና የባህር ላይ ንግድን በግንባር ቀደምትነት ስትመራ የኖረች ታላቅ ሀገር መሆኗ ሐቅ ነው።

ተፈጥሮም ቢሆን በመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ ለቀይ ባህርና ለኤደን ባህረ ሰላጤ እጅግ ቅርብ ያደረጋት ቢሆንም፣ በታሪካዊ አጋጣሚዎችና በፖለቲካዊ ሴራዎች ምክንያት ላለፉት ሶስት አሥርት ዓመታት በላይ ሰፊ ሕዝብና ግዙፍ ኢኮኖሚ ይዛ ያለ ባህር በር እንድትቀጥል ተገዳለች።

የጥንቱ የአክሱም ስልጣኔ ከዘመኑ የዓለም ሀያል መንግስታት ተርታ እንዲሰለፍ ምክንያት የሆነው አቅም የተገኘው ጠንካራ የባህር ኃይል በማደራጀት ከህንድ እስከ ሮማውያን ድረስ ያለውን ዓለም አቀፍ ንግድን መቆጣጠር በመቻሉ ነበር።

ዛሬ ላይ ሆነን ይህንን ታሪክ ስንመለከት ኢትዮጵያ እና ባህር በታሪክ የተዋሃዱ እንጂ ፈጽሞ የተነጣጠሉ እንዳልሆኑ ታሪክ በጉልህ ይመሰክራል።

ይሁን እንጂ ከ130 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ያላት፣ የኢኮኖሚ አቅሟ እያደገ የመጣው እና የብሪክስ አባል የሆነችው ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሆና መቀጠሏ በየትኛውም ሚዛን ፍትሓዊ አይደለም።

በየዓመቱ ለወደብ አገልግሎት በቢሊየኖች ዶላር የሚገመት ከፍተኛ ወጪ የምትከፍለው ኢትዮጵያ የባህር በር አልባነቷ ለኢኮኖሚዋ ዕድገት መሰናክል ሆኖባታል።

ኢትዮጵያ በሴራ ያጣችውን የባህር በር በማግኘት የጂኦግራፊ እስረኛ መሆኗ ማብቃት አለበት የሚል የጸና አቋም የያዘው የመደመር መንግሥት ይህንን የህልውና ጥያቄ ለመመለስ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን ሁሉ  እየተጠቀመ ነው።

በዚህም የጋራ ልማት፣ የጋራ ተጠቃሚነት እና የንግድ ልውውጥን መሰረት ያደረገ የሰላም መንገድ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን መንግስት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።

የባህር በር ለኢትዮጵያ ከንግድ ማሳለጫነት ባለፈ የብሔራዊ ደህንነት፣ የሉዓላዊነት እና የጂኦፖለቲካዊ ሚዛን መጠበቂያ አቅሟ ነው።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ይገባዋል፡፡
በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.