“ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ሌሎች ሀገራት በሚያዩን ልኬታና ከፍታ እራሳችንን እንድንመለከት እማጸናለሁ” – ፕሬዚዳንት ታዬ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ሌሎች ሀገራት በሚያዩን ልኬታና ከፍታ እራሳችንን እንድንመለከት እማጸናለሁ ሲሉ መላ ኢትዮጵያውያንን ጠይቀዋል፡፡
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት ÷ የምክክር ጉባዔው ስኬት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል ውስጥ አዲስ ጎዳና ነው፡፡
የምክክሩ ሒደት የሁላችን የሆነችውን ኢትዮጵያ የሚገልጡና የሚያጸኑ እንዲሁም የጋራ መሻትን፣ ርዕይና ዕጣ ፈንታን በአንድ ላይ ማራመድ የሚያስችሉ ሃሳቦች የተንሸራሸሩበት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ የሚስተዋለውን በተቃርኖ የተሞላ የፖለቲካ ባህል በመስበር ልዩነቶች ለጋራ ጥቅም የሚውሉበትና ዘመን ተሻጋሪ አዲስ ሃሳብ የሚወለድበት ሒደት እንዲሳለጥ መደላድል መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ጉዞ መስቀለኛ ሳይሆን ቀጥተኛ፣ ርቱዕና ብርቱ የሆነ የእድገትና የሕብረት መንገድ ብቻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የምክክሩ ግብ ጊዜያዊ የፖለቲካ መድህን ማግኘት ሳይሆን ለሀገር እድገት የሚበጅ ትጉህ ርምጃ እና ዘላቂ ፍኖትን መተለም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የሀገር ብርታት ጥበብና ብልሃቱ ምክክር ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ ÷ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው ኢትዮጵያን ለማጽናት የሚያስችል ታሪካዊ ሒደት ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያንን ልዩ የሚያደርገን ሕልውናችንን የሚፈታተኑ ነገሮች ሲያጋጥሙን ሀገር እየጠበቅንና እየመከርን ሀገራችንን ማጽናት መቻላችን ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡
የዚህ መሰረቱ ደግሞ ኢትዮጵያ የጋራና የሁላችንም ስልጣኔ እውቀትና እውነትን አጋምዳ የያዘች በመሆኗ ነው ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ በመልዕክታቸው ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ሌሎች ሀገራት በሚያዩን ልኬታና ከፍታ እራሳችንን እንድንመለከት እማጸናለሁ ሲሉም መላ ኢትዮጵያውያንን ጠይቀዋል፡፡
እውነትን ለመያዝና ለመፈጸም፣ ምንጊዜም እውነት ትክክለኛ ጊዜ እንደምትሻ ሁሉ በዚህ አዲስ ምዕራፍ ለሀገርና ሕዝብ ለእውነት መታመን ያለው የሞራል ኃላፊነት ከፍ ያለ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ