Fana: At a Speed of Life!

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ለማጠናከር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ፡፡
በክልሉ የ2019 የተቀናጀ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ንቅናቄ በከንባታ ዞን በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል፡፡
በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ በክልሉ ግብርናን በማዘመን ያለውን እምቅ ጸጋ ወደ ሃብት ለመቀየር እየተሰራ ነው፡፡
ለዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን አስረድተዋል፡፡
በቀጣይ የሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ይበልጥ ለማጠናከር ትኩረት መደረጉን ጠቁመው ÷ ለዚህም የዝርያ ማሻሻያ እና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ ባለፉት ሶስት ዓመታት የእንስሳት ዘርፉን ለማዘመን በተሰሩ ሥራዎች 8 የወተት ማቀነባበሪያዎች መቋቋማቸውንና በዚህም ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
በ2015 በጀት ዓመት 321 ሚሊየን ሊትር የነበረው ዓመታዊ የወተት ምርት በ2018 መጨረሻ ላይ 725 ሚሊየን መድረሱን አመልክተዋል፡፡
ለዚህ ከፍተኛ የምርት እድገት የእንስሳት ዝርያ ማሻሻል ተግባር ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ ነው አቶ ኡስማን ሱሩር ያስገነዘቡት፡፡
የዝርያ ማሻሻል ሥራ በክልል ደረጃ 14 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱን ገልጸው ÷ ይህም ለምርታማነት መጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል፡፡
የቢሮው ምክትልና የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ እያሱ ተረፈ በበኩላቸው÷ ዓመታዊ የወተት ምርትን ወደ 805 ሚሊየን ሊትር ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ከዛሬው ዕለት ጀምሮ 287 ሺህ ላሞችን የማዳቀል ሥራው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በቁርጠኝነት እንደሚከናወን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.