Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለ1501ኛው የነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) የመውሊድ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ያስተላለፈው መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሀገር ውስጥ እና በመላው ዓለም ለሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለ1 ሺህ 5መቶ አንደኛው የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት (መውሊድ) መታሰቢያ በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን በአክብሮት ይገልፃል፡፡

የዘንድሮው የመውሊድ በዓል የሚከበረው ሀገራዊ ምክክሩ በስኬት በተጠናቀቀበት ማግስት በመሆኑ የመታሰቢያ በዓሉን ደስታ እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡

ለአንድ ወር ከ15 ቀናት ሲካሄድ የነበረው ሀገራዊ ምክክር ጠንካራ ክርክር፤ የሀሳብ እና የፍላጎት ልዩነት የታየበት ቢሆንም በሂደት ግን የሀገርን እና የሕዝብን ጥቅም በማስቀደም በመግባባት የተጠናቀቀ ታሪካዊ ስኬት ነው፡፡

ለሀገራዊ ምክክር ስኬት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እና አገልጋዮች ያበረከቱት አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ በቀጣይም ስምምነቶቹን በተግባር ከመተርጎም አንፃር ኃላፊነታቸውን በተግባር እንደሚወጡ እምነታችን የጸና ነው፡፡

እንደሚታወቀው የዚህ ዓመት መውሊድ “የፍትሑ ነብይ” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ይሆናል፡ ፡ መሪ ቃሉ ነብዩ ሙሀመድ ለፍትህ የላቀ ትኩረት ሰጥተው እንደኖሩ እና እንዳገለገሉ ለማሰብ፣ ለማሰላሰል እና ለማውሳት እድል የሚሰጠን ነው፡፡

የነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) መወለድ በምድር ላይ ሰፍኖ የነበረውን ኢሰብአዊነት፣ በደል፣ ሀጢአትና ርኩስት ለማረም እና ለማስወገድ ሚናው የጎላ ነው፡፡ ሰብአዊ ክብርና ሰብአዊ ርህራሄ በምድር ላይ በሙላት ይሰፍንም ዘንድ ነው፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን ሰዎች የመፈጠራቸውን ዋና ዓላማ እንዲረዱና ምድራዊ ሕይወታቸውን በጥቃቄ እንዲመሩ መንገድ የጠረገም መሆኑም ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ሰዎች አላህን በመፍራት እንዲኖሩ ያስቻለ በመሆኑ የመልዕክተኛውን የልደት በዓል ስናከበር ፈጣሪ ለዋለልን ውለታ ምስጋና በማቅረብ፣ የእሳቸውን ታላቅ ታሪክ በመዘከር በተለይም ለፍትህ የከፈሉትን ዋጋ በማሰብ እና እኛም ፍትህ በምድራችን በሙላት ይሰፍን ዘንድ የበኩላችንን ኃላፊነት ለመወጣት ቃል በመግባት ሊሆን ይገባል፡፡

እዚህ ላይ ነብዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) በዚህ ምድር በኖሩበት ዘመናት ሁሉ ለወገኖቻቸው ብቻ ሳይሆን ለሰው ዘር በሙሉ ሰብአዊነትን፣ ፍቅርን፣ አክብሮትን እና ርህራሄን ያሳዩ እንደነበርማስታወስ ተገቢ ይሆናል፡፡

በመጨረሻም 1 ሺህ 5መቶ አንደኛውን የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) የልደት መታሰቢያ ክብረ በዓል ስናከብር በተለመደው ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህላችን መሰረት በሕመም አልጋ ላይ፣ በሕግ ጥላ ስር በአጠቃላይም በችግር ውስጥ የሚገኙትን ወገኖቻችንን በመጠየቅ እና በማበረታታት፣ ያለንን በማካፈል ሊሆን ይገባል፡፡

በተያያዘም ለአገራችን ኢትዮጵያ ሰላም፣ ለሕዝባችን አንድነት እና በረከት ከልብ የሆነ ዱዓ በማድረግ እንዲሆን በታላቅ አክብሮት ጥሪ እያቀረብን በድጋሜ ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች፣ በየደረጃው ለሚገኙ መሪዎች እና ተከታዮች በሙሉ እንኳን ለታላቁ ነብይ ለነብዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) 1 ሺህ 5መቶ አንደኛው የልደት ክብረ በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳችሁ፣ በዓሉ የሰላም፣ የጤና፣ የደስታ፣ የተስፋ እና የበረከት እንዲሆንላችሁ ከልብ እንመኛለን፡፡

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.