የለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ላይ እያየን ያለው ለውጥ ከሁሉ የሚልቅ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በከተማችን ላይ ከሚታየው ለውጥ ሁሉ የሚልቀው የለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ላይ እያየን ያለው ለውጥ ነው አሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ።
ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ፥ ዛሬ የልጆች ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን (CIFF) መስራች እና የቦርድ ሃላፊ ክሪስ ሆን እና ቡድናቸውን ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከልን አስጎብኝተናል ብለዋል።
“ከምንሰራቸው ስራዎች ሁሉ ትልቁ ስራ በሰው ላይ የምንሰራው፣ በተለይም በሴቶች ላይ የምንሰራው ነው” የሚለውን የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መልዕክት የስራችን ማዕከል አድርገን እየፈፀምን እንገኛለን ነው ያሉት።
ከንቲባዋ ለነገዋ ጅማሮው በተለያዩ ማህበራዊ ችግር ውስጥ ያሉ ሴቶች እህቶቻችን ተስፋና እድላቸው እንዲለመልም ፣ ክብራቸውና ደህንነታቸው ተጠብቆ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ከልብ በመነጨ ስሜት የተፀነሰ፣ ተፀንሶም ወደ ተግባር የተቀየረ ትልቅ ራዕይን የሰነቀ ስራ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
በዚህም ለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በ2016 ዓ.ም ጀምረነው በ5 ዙር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች 3,259 ሰልጣኞችን በክህሎት እና በስብዕና ግንባታ አሰልጥነን ወደ ስራ አሰማርተናል ብለዋል።
ዛሬ ሁሉም ተመራቂዎች ክብር ያለው ኑሮ፣ ብሩህ ተስፋን ሰንቀው አዲስ ህይወት መኖር ጀምረዋል ያሉት ከንቲባ አዳነች ለ”ለነገዋ የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል” የሰነቅነው ራዕይ፣ በዓመት እስከ 10 ሺህ ሴቶችን የሚያበቃ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንዲሁም አካታች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ልምድ የሚቀሰምበት የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ማስቻል ነው ሲሉ አክለዋል።
ይህ ራዕይ በተሟላ ሁኔታ እንዲተገበር ሊደግፋን የመጡት የልጆች ኢንቨስትመንት ፈንድ ፋውንዴሽን (CIFF) መስራች ክሪስን በለነገዋ የሴቶች የተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል የምንሰራቸው ሰው ተኮር ስራዎች አስጎብኝተን በቀጣይም በጋራ በምንሰራቸው ስራዎች ዙሪያ ተወያይተናል ነው ያሉት።