ለዘመናት በስኬት የዘለቀው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ በስኬት የታጀበ የውጭ ግንኙነት ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡
ከቀደሙት ነገስታት ጀምሮ በቅርብም ሆነ ሩቅ ካሉ የዓለም ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ጠንካራ የውጭ ግንኙነቶችን መስርታ ብሔራዊ ጥቅሞቿን እያስጠበቀች እስከ ዛሬ ዘልቃለች፡፡
እ.ኤ አ በ1920ዎቹ አፍሪካውያን እህት ወንድሞቻችን በቅኝ ግዛት በሚማቅቁበት ወቅት ኢትዮጵያ የዓለም መንግስታት ማህበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) አባል መሆን ችላ ነበር፡፡
በኋላም የተባበሩት መንግሥታትን በመስራችነት የተሳተፈች ሃገር ስትሆን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ላይም የአሰባሳቢነትና የመሪነት ሚና ተጫውታለች፤ በዚህ ታሪካዊ ሚናዋ ነው የአህጉሪቱ ግዙፍ ተቋም መቀመጫ ለመሆን የቻለችው፡፡
የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ከዓለም ጋር ያለንን ግንኙነት የምንቃኝበትና የምንበይንበት ቁልፍ መሳሪያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ገለልተኛ የሆነና ወዳጅ ማብዛትን መሰረት ያደረገ ፖሊሲን ትጠቀማለች፡፡
እነዚህ የውጪ ግንኙነት ፖሊሲዎቿን ስትቀርፅ ደህንነቷ ማስጠበቅ፣ ኢኮኖሚዋን ማሳደግ በጠቅላላው ብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነቷን መነሻና መድረሻ በማድረግ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ዓለም በኃይል ሚዛን ፉክክሮች እና ሽኩቻዎች ተወጥራለች፡፡ በዚህም የብዝሃ ዋልታ ስርዓት (መልቲ ፖላር) ለማዋለድ በሚደረግ የኃያላን ፉክክር እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡
በዚህም ውስጥ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥሩ ሁለትዮሽና የብዝሃ ወገን የውጪ ግንኙነቶችንና ትብብሮችን ታካሂዳለች፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ለየትኛውም ጎራ ያላደላ ገለልተኛ ዲፕሎማን ትከተላለች፡፡
በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ በልማት፣ በወታደራዊ፣ በደህንነት፣ በኃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂ እና በመሳሰሉት ዘርፎች ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ተፈራርማለች፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ቅድሚያ በመስጠት በልማት፣ ሰላምና ጸጥታ ዙሪያ በልዩ ትኩረት ትሰራለች፡፡
በመሆኑም የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራትን፣ የኢኮኖሚ ትስስሮችን ማጠናከርን፣ በቀጣናው ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ በጋራ መስራት የሚያስችል ቀጣናዊ ጥምረትን ታደርጋለች፡፡
በቤተልሔም ግርማ