ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን በሰላማዊና አካታች በሆነ መንገድ እርስ በርስ እንዲደማመጡ ዕድል ፈጥሯል – የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን በሰላማዊና አካታች በሆነ መንገድ እርስ በርስ እንዲደማመጡ ዕድል ፈጥሯል አለ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በሰጠው መግለጫ ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን በሰላማዊና አካታች መንገድ እርስ በርስ እንዲደማመጡ፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲወያዩ፣ መግባባትን እንዲፈጥሩና የጋራ መፍትሔዎችን እንዲፈልጉ መልካም ዕድል ፈጥሮ መጠናቀቁ ለኢትዮጵያ ወሳኝ የሆነ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን ገልጿል፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ተሳታፊ አንደነበሩ በመጠቆም በአመካካሪነት፣ በተሳታፊነት፣ ለኮሚሽኑ በአማካሪነት፣ በታዛቢነት፣ በባለሙያዎች ቡድን አባልነት እንዲሁም ስለምክክሩ ግንዛቤ በመፍጠርና በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ የአጀንዳ ግብዓቶችን በመስጠት የተጫወቱት ሚና የሲቪል ማህበረሰቡ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ገንቢና ኃላፊነት የተሞላበት አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችል ያረጋገጠ መሆኑን አመልክቷል።
ከሂደቱ ብዙ የተማርን ሲሆን በዋነኛነት፣ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገንቢ፣ አካታችና አስቻይ የሥራ ከባቢ ሲፈጠርላቸው በሀገራዊ ሂደቶች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የጎላና ውጤታማ እንደሚሆን ነው የገለጸው።
የሲቪል ማህበረሰቡ ጥንካሬ ከህብረተሰቡ ጋር ባለው ቀጥተኛ ቅርበት፣ በሚወክላቸው የተለያዩ አመለካከቶች፣ በሙያዊ እውቀቱ እና ዜጎችን ከተቋማት ጋር በማገናኘት ባለው አቅም ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጠቁሟል።
የሲቪል ማህበራት ቀጣዩና የበለጠው ወሳኝ ተግባር የምክክሩን ምክረ ሃሳቦች ወደ ተጨባጭ ርምጃ መቀየር፣ የሕዝብ ተሳትፎን ማስቀጠል፣ መተማመንን ማጠናከር እና ልዩነቶች በግጭት ወይም በኃይል ሳይሆን በውይይትና በምክክር የሚፈቱበትን ባህል ማሳደግ መሆኑን አንስቷል።
ስለሆነም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በነጻነት፣ በኃላፊነትና በውጤታማነት ለሀገራዊ ምክክሩ ምክረ ሃሳቦች አፈጻጸም፣ ለሰላም ግንባታና ለዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ፣ አጋዥና ገንቢ የሆነ የሲቪክ ምህዳር እንዲጠናከር ጥሪ አቅርቧል።
ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያውያን የመነጋገር፣ የመደማመጥ፣ ያላግባቧቸውን ጉዳዮች ሁላችንንም ተጠቃሚ ባደረገ መንገድ የመፍታት አቅም እንዳላቸው አሳይቷል።
አሁን ያለብን የጋራ ኃላፊነት ይህንን የምክክር ባህል ማስቀጠልና የምክክሩን ውጤት ወደ ሰላማዊ፣ አካታችና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ግንባታ መቀየር መሆኑን አስገንዝቧል፡፡
የሲቪል ማህበራት በዚህ ሀገራዊ ምክክር ያሳዩትን ቁርጠኝነት በቀጣይ ሀገራዊ ሂደቶች እንደሚደግሙት አመልክቷል፡፡
ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም መካሄድ የጀመረው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም መካሄዱ ይታወሳል፡፡