Fana: At a Speed of Life!

ለመድፈኞቹ ተስፋን የፈነጠቀው ክሪስቶስ ዞሊስ…

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ግሪካዊው የ24 ዓመት የመስመር ተጫዋች ክሪስቶስ ዞሊስ በአርሰናል የጀመረው አዲስ የእግር ኳስ ምዕራፍ በጥሩ አጀማመር ተውቧል።
ተጫዋቹ በ2026/27 የፕሪሚየር ሊግ መክፈቻ ጨዋታ አርሰናል ኮቨንትሪ ሲቲን 3 ለ 0 ሲያሸንፍ፤ ለቡካዮ ሳካ የግብ እድል በመፍጠር ትኩረት ስቧል።
ዞሊስ የእግር ኳስ ሕይወቱን በግሪኩ ፓኦክ አካዳሚ አጎልብቶ ወደ ዋናው ቡድን በመድረስ በወጣትነቱ ራሱን ማሳየት ጀመረ። በፓኦክ ቆይታው በሁሉም ውድድሮች በ57 ጨዋታዎች 17 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
የፓኦክ ብቃቱ ድንበር ተሻግሮ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አቅሙን ለማሳየት መንገድ ከፍቶለታል፡፡
በፈረንጆቹ 2021 ወደ ኖርዊች ሲቲ ተዛወረ። ሆኖም በእንግሊዝ ያሳለፈው የመጀመሪያ ጊዜ ቀላል አልነበረም፤ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የመሰለፍ በቂ እድል ባለማግኘቱ በውሰት ወደ ኤፍሲ ቴዌንቴ እና ፎርቱና ዱሰልዶርፍ አመራ፡፡
ዞሊስ በፎርቱና ዱሰልዶርፍ ያሳለፈው የ2023/24 የውድድር ዘመን የሕይወቱ አስፈላጊ የለውጥ ወቅት ነበር። ለቡድኑ በ30 ጨዋታዎች የተሰለፈ ሲሆን፤ 22 ግቦች እና 6 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማስመዝገብ ግብ አስቆጣሪነቱንና የፈጠራ ችሎታውን አሳየ።
በፈረንጆቹ 2024 ወደ ቤልጂየሙ ክለብ፤ ክለብ ብሩዥ በመዛወር በመጀመሪያው የውድድር ዘመን 16 የሊግ ግቦችን እና 9 የግብ እድሎችን የፈጠረው ዞሊስ በ2025/26 የውድድር ዘመን በቤልጂየም ሊግ 36 ጨዋታዎች ላይ 17 ግቦችን እና 23 የግብ እድሎችን በመፍጠር 40 የግብ አስተዋፅዖዎችን አስመዝግቧል።
አርሰናል ዞሊስን ሲያስፈርም በግራ መስመር በኩል የነበረበትን ክፍተት በተለይም ፍጥነት፣ የግብ አስተዋጽኦ እና የፈጠራ ችሎታው የላቀ ተጫዋቸን በማምጣት ቦታውን ለማጠናከር በማሰብ ነው፡፡
ተጫዋቹ በብሩዥ ያሳየው የግብና የግብ እድሎችን የመፍጠር ቁጥር እንዲሁም በአውሮፓ ውድድሮች ያገኘው ልምድ ለአርሰናል ተመራጭ አድርጎታል።
ክሪስቶስ ዞሊስ በቅድመ ውድድር ዝግጅት ጨዋታዎች፣ በኮሚኒቲ ሺልድ ጨዋታ እንዲሁም በሊጉ በኮቨንትሪ ላይ ያሳየው ብቃት ተጫዋቹ በመድፈኖቹ ቤት አጀማማሩን አሳምሮለታል፡፡
በጨዋታው ከሳካ ጋር የፈጠረው ግንኙነት እና በግራ መስመር ያሳየው እንቅስቃሴ የአርሰናል የማጥቃት መስመር ተጨማሪ ኃይል እንዳገኘ ያመላክታል።
ፍጥነት፣ አካላዊ ብቃት፣ ብሃት እዲሁም የላቀ ውሳኔ አሰጣጡ ከቡድኑ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ አድናቆትን አስገኝቶለታል፡፡
ነገር ግን የዞሊስን በአርሰናል የሚኖረውን ስኬት በአንድ ጨዋታ ብቻ መመዘን አይቻልም። ፕሪሚየር ሊግ ከቤልጂየም ሊግ በተለየ መልኩ ፈጣን፣ አካላዊ እና በትንሽ ስህተት የሚቀጣ ውድድር ነው። ስለዚህ ዞሊስ በብሩዥ ያሳየውን የግብ አምራችነት ብቃት በእንግሊዝ ማስቀጠል ዋናው ፈተና ይሆናል።
የክሪስቶስ ዞሊስ የእግር ኳስ ጉዞ በአንድ ሌሊት የተፈጠረ ስኬት አይደለም። ከግሪክ ወጣት አካዳሚ ተጫዋችነት ተነስቶ በፓኦክ፣ ኖርዊች፣ ቴዌንቴ፣ ዱሰልዶርፍ እና ክለብ ብሩዥ በኩል አልፎ ዛሬ አርሰናል ደርሷል።
የእርሱ ታሪክ ችሎታ ብቻ ሳይሆን ከአስቸጋሪ ወቅቶች በኋላ መመለስና ራስን እንደገና ማረጋገጥ የሚቻል መሆኑንም የሚያሳይ ነው።
ዞሊስ ለግሪክ ብሔራዊ ቡድን እስካሁን ድረስ 32 ጨዋታዎችን አድርጎ 9 ግቦችን አስቆጥሯል።
ከፓኦክ የተነሳው እና በብሩዥ የፈነጠቀው የግሪክ ተስፈኛ አሁን በአርሰናል ታሪክ ውስጥ የራሱን ስም ለመጻፍ በር ተከፍቶለታል።
የመጀመሪያው ጨዋታ ጥሩ ምልክት ሰጥቷል፤ ቀጣዩ ፈተና ግን ይህንን ብቃት በተከታታይ ጨዋታዎች ማረጋገጥ ነው።
በአቤል ነዋይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.