Fana: At a Speed of Life!

የሲዳማ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በትብብር ለመስራት ተስማማ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሲዳማ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሻሸመኔ ፋና ኤፍ ኤም 103 ነጥብ 4 ጋር በትብብር ለመስራት ተስማምቷል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ መንግስቱ ማቲዎስ በስምምነት ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት ÷ በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ሻሸመኔ ፋና ኤፍ ኤም የሚተላለፉ ፕሮግራሞች የክልሉ ሕዝብ በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሃሳቡን እንዲያቀርብ እድል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡

የሚሰራጩ ፕሮግራሞች ተቋማት መንግሥት ባስቀመጠው የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ ሕዝቡን እያገለገሉ ስለመሆኑ የሚገነዘቡበት፣ ከሚሰጡ የሕዝብ አስተያየቶች እርማት የሚወስዱበትና የሥራቸውን ደረጃ የሚያዩበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሻሸመኔ ፋና ኤፍ ኤም በቀጥታ የሬዲዮ ውይይት ላይ የሚመለከታቸው ተቋማት በአካል በመገኘት የክልሉ ሕዝብ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በማዳመጥ ምላሽ የሚሰጡበትና ለቀጣይ ሥራዎች አቅጣጫ የሚያስቀምጡበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ በሬዲዮ ውይይት መድረኩ በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው አመራሮች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት እድል መፍጠሩን ነው ያነሱት፡፡

በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሻሸመኔ ፋና ኤፍ ኤም 103 ነጥብ 4 ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢቂላ ቱፋ በበኩላቸው ÷ በሁለቱ ተቋማት መካከል የተደረሰው ስምምነት በክልሉ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሳለጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የክልሉ ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች በሃሳብ መድረኮች የሚሳተፉ መሆኑን ጠቁመው ÷ ይህም የክልሉ ሕዝብና መንግሥት በበለጠ እንዲቀራረቡ እንዲሁም ዘመናዊ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲገነባ እድል የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ፋና ኤፍ ኤም 103 ነጥብ 4 በሁሉም ዘርፎች የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የክልሉን ሕዝብና መንግሥት በቀጥታ የሬዲዮ ውይይት መርሐ ግብር ለማገናኘት ይሰራል ብለዋል፡፡

ጣቢያው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሕዝብን አሳታፊ የሚያደርጉ መሰናዶዎችን በማዘጋጀት የካበተ ልምድ እንዳለው ያወሱት አቶ ቢቂላ ÷ የዛሬው ስምምነት ደግሞ ሥራዎቹ በበለጠ እንዲጠናከሩ የሚረዳ ነው ብለዋል።

ጣቢያው የለውጥ ሃሳቦች እንዲጎለብቱ እና በየተቋማቱ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዲፈቱ በትጋት እንደሚሰራም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በብርሃኑ በጋሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.