Fana: At a Speed of Life!

የግብርናው ሞተር፡ የጎዴው ግዙፉ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ምድር ግብርና የኢኮኖሚው ጀርባ አጥንት እና የብዙሃኑ ህዝብ የኑሮ መሠረት ቢሆንም፣ የዘርፉ ምርታማነት ግን ለብዙ አሥርት ዓመታት በውጭ ሀገር ግብዓቶች ላይ ጥገኛ ሆኖ ቆይቷል።

በተለይም ለአፈር ለምነትና ምርታማነት ቁልፍ ሚና ያለውን ማዳበሪያ ከውጭ ሀገር ማስገባት፣ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ ለዓለም አቀፍ የገበያ መዋዠቅ እና ለወቅት መዛባት ሲዳርጋት የኖረ አሳሳቢ ፈተና ነው።

ታዋቂው አሜሪካዊ ሳይንቲስት፤ የኖቤል ሰላም ሽልማት አሸናፊ እና የአረንጓዴው አብዮት አባት ኖርማን ቦርሎግ (ዶ/ር) “Feeding a Hungry World: Fertilizer, Nutrition, and the Green Revolution” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደፃፉት፡-“አንድ ሀገር የራሷን የአፈር ማዳበሪያ የማምረት የኢንዱስትሪ አቅም ከሌላት፣ የግብርና አብዮት ማምጣትም ሆነ ህዝቦቿን ከረሃብ ሙሉ በሙሉ መታደግ አይቻላትም፤ ማዳበሪያ የምግብ ዋስትናን ለመጠበቅ የሚያገለግል የፖለቲካዊ እና የኢኮኖሚያዊ ነፃነት መሣሪያ ነው።”

ለዚህም ነው የመደመር መንግሥት በሀገሪቱ የግብርናውን ዘርፍ የሚቀይር ግዙፍ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታን ያስጀመረው።

የዘመናት ጥገኝነት በዘላቂነት በመስበር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የታለመውና በሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ እየተገነባ ያለው ግዙፍ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የሀገሪቱን የግብርና ታሪክ እና ቀጣናዊ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ታሪካዊ ክስተት ነው።

በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር የሚጠይቀው ይህ ሜጋ ፕሮጀክት፣ የሀገሪቱን የተፈጥሮ ሀብት ለዘላቂ ልማት ለማዋል የተወጠነ ስትራቴጂካዊ ርምጃ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል ከአፍሪካ ቀዳሚው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ ጋር በመተባበር የሚያስገነባው ይህ ፋብሪካ፣ በካልብ እና ሂላላ የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት በ110 ኪሎ ሜትር የቧንቧ መስመር በመዘርጋት ለኃይል እና ለጥሬ ዕቃነት ይጠቀማል።

ፋብሪካው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በዓመት 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ዩሪያ እና 2 ሚሊየን ቶን የናይትሮጅን፣ ፎስፈረስ እና ፖታሺየም ማዳበሪያ የማምረት አቅም ይኖረዋል፤ ይህም ከዓለማችን አምስት ግዙፍ የዩሪያ ማምረቻዎች አንዱ ያደርገዋል።

ይህ አህጉራዊ ተፅዕኖ ያለው የኢንዱስትሪ መሠረት፣ ለኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች የትውልድ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጥ ነው።

አርሶ አደሩ ማዳበሪያን በወቅቱ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ እና በበቂ ሁኔታ ባለማግኘቱ ምክንያት ለምርታማነት መቀነስ እና ለኪሳራ ይዳረግ የነበረበት ዘመን በዚህ ፕሮጀክት ያበቃል።

ምርቱ በሀገር ውስጥ መመረቱ አቅርቦቱን አስተማማኝ ከማድረጉም በላይ፣ የህዝብን የዕለት ጉርስ ከማረጋገጥ አልፎ ሀገር የራሷን ዕድል በራሷ የመወሰን መብት የምትጎናጸፍበት “የምግብ ሉዓላዊነት” ዋና መሣሪያ ይሆናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱን በጎበኙበት ውቅት “በኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን፣ በምግብ ዋስትና፣ በኢንዱስትሪ ዕድገት እና በኢኮኖሚያዊ ራስን መቻል ላይ የተደረገ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት ነው” በማለት የፕሮጀክቱን ከመሠረተ ልማት ግንባታ በላይ መሆን ጠቁመዋል።

የዳንጎቴ ግሩፕ ፕሬዚዳንት አሊኮ ዳንጎቴም “ይህ አጋርነት አፍሪካን በኢንዱስትሪ ለማዘመን እና በአህጉሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ያለንን የጋራ ራዕይ የሚያሳይ ነው፤ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ ቀዳሚዋ የግብርና ሀገር የመሆን አቅም አላት” በማለት የሀገሪቱን የወደፊት ብሩህ ተስፋ መስክረዋል።

በእርግጥም ኢትዮጵያን የምስራቅ አፍሪካ የግብርና እና የማዳበሪያ የንግድ ማዕከል እንደሚያደርጋት ይታመናል። በምግብ ምርት እና በግብርና ግብዓት ራሷን የቻለች ሀገር፣ በቀጣናዊ የፖለቲካ ድርድሮችም ሆነ በኢኮኖሚ ትስስር ላይ ያላት ተሰሚነት እና የጂኦፖለቲካ ተፅዕኖም በእጅጉ የጎላ ይሆናል።

በኃይለኢየሱስ መኮንን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.