Fana: At a Speed of Life!

በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አዲስ ታሪክ የጻፈው አፍሪካዊው ያያ ቱሬ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኮትዲቯራዊው የቀድሞ ኮከብ ተጫዋች ያያ ቱሬ በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ታሪክ የሚያሰለጥነውን ክለቡን ለምድብ ድልድል ያበቃ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አሰልጣኝ ሆኗል፡፡

ቱሬ የስሎቫኪያውን ክለብ ስሎቫን ብራቲስላቫን በማሰልጠን በአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ክለቡን ለምድብ ድልድል ያደረሰ የመጀመሪያው አፍሪካዊ አሰልጣኝ መሆን ችሏል፡፡

ስሎቫን ብራቲስላቫ በትናንትናው ዕለት ከስሎቬኒያው ኤንኬ ሴልዬ ጋር ባደረገው የማጣሪያ ጨዋታ በተጨማሪ ሰዓት 2 ለ 1 በማሸነፍ የሻምፒየንስ ሊጉን የምድብ ድልድል ተቀላቅሏል፡፡

ይህ ድል ያያ ቱሬን በአፍሪካ እግር ኳስ ታሪክ ልዩ ቦታ ላይ አስቀምጦታል።

ከዚህ በፊት በርካታ አፍሪካውያን አሰልጣኞች ክለቦቻቸውን በሻምፒየንስ ሊግ የማጣሪያ ዙሮች መርተው ቢያልፉም፣ አንዳቸውም ወደ ውድድሩ የምድብ ድልድል ማለፍ አልቻሉም።

ቱሬ ይህንን ታሪካዊ ውጤት ማሳካት ችሏል።

የቱሬን ስኬት ይበልጥ ልዩ የሚያደርገው ዋና አሰልጣኝነት የመጀመሪያ ሥራው መሆኑ ነው።

የኮትዲቯር ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ ተጫዋች ቱሬ በተጫዋችነት ዘመኑ በሻምፒየንስ ሊግ ታላቅ ታሪክ ሰርቷል። በፈረንጆቹ 2009 ከባርሴሎና ጋር የውድድሩን ዋንጫ አንስቷል።

ያያ ቱሬ በተጫዋችነት ዘመኑ አራት ጊዜ የአፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች ተብሎ የተመረጠ ሲሆን ÷ በሐምሌ ወር ስሎቫን ብራቲስላቫን በዋና አሰልጣኝነት መቀላቀሉ ይታወሳል።አሁን ደግሞ በተጫዋችነት ያሳለፈውን የሻምፒየንስ ሊግ ተሞክሮ በአሰልጣኝነት በመድገም አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል።

የያያ ቱሬ ድል የግል ስኬት ብቻ አይደለም ፤ የአፍሪካ እግር ኳስ በአውሮፓ እግር ኳስ ትልቁ መድረክ ላይ እያሳየ ያለውን እድገት፣ ተፅዕኖ እና ተሳትፎ የሚያሳይ ታላቅ ምልክት ጭምር እንጂ፡፡

ቱሬ በተጫዋችነት ያሳየውን ብቃት በአሰልጣኝነቱም ማሳየት መጀመሩ ለሌሎች አፍሪካዊ አሰልጣኞች ትልቅ መነሳሳት እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.