ኢትዮጵያ እንደ ሕዳሴ ግድብ የባሕር በር ጥያቄዋንም ማሳካት የምትችል ታላቅ ሀገር ናት – ኡስታዝ ጀማል በሽር
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እንደ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሁሉ የባሕር በር ጥያቄዋን በውጤታማነት ማሳካት የምትችል ታላቅ ሀገር ናት አሉ የዓባይ ንጉሶች ሚዲያ ባለቤት ኡስታዝ ጀማል በሽር።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሀገሪቱ የውሃ ሀብቶቿን በራሷ አቅም አልምታ መጠቀም እንደምትችል በግልጽ ያሳየ ታላቅ ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል።
ኡስታዝ ጀማል እንዳሉት÷ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ቀጣናውን በኤሌክትሪክ ኃይል በማስተሳሰር የትብብር መንገዶችን ከማጠናከር አኳያ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ያላት ትብብር ሁልጊዜም በጋራ ተጠቃሚነትና በሰላማዊ ልማት ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በተግባር ማሳየቱንም ጠቁመዋል።
ሀገሪቱ የውሃ ሀብቷን እንዳትጠቀም የሚከለክላት ማንም አካል እንደሌለ የገለጹት ኡስታዝ ጀማል የኢትዮጵያ የመልማት መብት ዓለም አቀፍ ሕጎችን እና መርሆዎችን ፍጹም ያከበረ መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይ ሊከናወኑ የታቀዱ የልማት ስራዎች ሀገሪቱን ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ መሆናቸውን አንስተው እየተጠናቀቁ ያሉ የመስኖ ግድቦች፣ አብዛኛው ስራ የተጠናቀቀው የኮይሻ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት እና ሌሎች ስራዎች የኢትዮጵያን የልማት ውጥን እውን እያደረጉት ይገኛሉ ብለዋል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በሁሉም መስኮች ያሰበቻቸውን ግቦች እያሳካች መሆኑን ጠቅሰው በከተማ ልማት፣ በቱሪዝም እንዲሁም በምክክር የመግባባት ዴሞክራሲን በመገንባት ረገድ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን አብራርተዋል።
አሁን ላይ የኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅም ዋነኛ ጉዳይ የሆነው የባሕር በር ጥያቄ በይፋ መነሳቱን በማስታወስ የባሕር በር ጥያቄ የህልውና ጉዳይ እና በፍትሃዊነት የመልማት ጥያቄ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
ይህንን ታሪካዊ ጥያቄ ማሳካት የትውልዱ የማይቀር እውነት መሆኑን አንስተው ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘቷ አይቀሬ መሆኑን ጠላት ሳይቀር እየመሰከረ ያለው እውነት ነው ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ኢትዮጵያ እንደ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች ታላላቅ ፕሮጀክቶችም የባሕር በር ጥያቄዋን በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ማሳካት የምትችል ጽኑ መሰረት ያላት ሀገር ናት ሲሉም ተናግረዋል፡፡