Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ በሀገሪቱ የንግድ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ስኬት ተመዝግቧል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ተግባራዊ ባደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ በሀገሪቱ የንግድ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ስኬት ተመዝግቧል አለ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ላይ ከፍተኛና ታሪካዊ እድገት እንዲመዘገብ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።
በ2018 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከወጪ ንግድ 11 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ገቢ በማግኘት የዕቅዱን 119 ነጥብ 14 በመቶ ማሳካት መቻሉ ነው የተገለጸው፡፡
በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከወጪ ንግድ 9 ነጥብ 40 ቢሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ 11 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር ሆኖ መመዝገቡ ተመላክቷል፡፡
የማዕድን ዘርፍ 5 ነጥብ 07 ቢሊየን ዶላር ገቢ በማስመዝገብ የዕቅዱን 152 ነጥብ 75 በመቶ በማሳካት ቀዳሚውን ስፍራ ይዟል፡፡
በግብርና ምርቶች 3 ነጥብ 83 ቢሊየን ዶላር ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ ይህም የዕቅዱን 90 ነጥብ 01 በመቶ መሸፈኑ ተጠቁሟል፡፡
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 493 ነጥብ 55 ሚሊየን ዶላር ወይም 93 ነጥብ 80 በመቶ አፈጻጸም አስመዝግቧል፡፡
የኤሌክትሪክና ሌሎች ዘርፎች 425 ነጥብ 45 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማስገኘታቸው ነው የተገለጸው፡፡
የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ከ2017 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በሁሉም ዘርፎች ላይ ተስፋ ሰጪ ዕድገት አሳይቷል፡፡
የማዕድን ዘርፍ የ2 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር (71 ነጥብ 18 በመቶ) ከፍተኛ ጭማሪ ሲያሳይ፣ የግብርና ዘርፍ የ238 ነጥብ 24 ሚሊየን ዶላር (6 ነጥብ 64 በመቶ) ዕድገት አስመዝግቧል፡፡
እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 45 ነጥብ 68 ሚሊየን ዶላር፣ የኤሌክትሪክና ሌሎች ዘርፎች ደግሞ 115 ነጥብ 41 ሚሊየን ዶላር (37 ነጥብ 22 በመቶ) ጭማሪ ማሳየቱ ተገልጿል።
ለዚህ ታሪካዊ የወጪ ንግድ ገቢ ዕድገት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ውጤታማ አተገባበር በዋነኝነት የሚጠቀስ ነው፡፡
የገበያ ትስስርና ፖሊሲ፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና መመሪያን አጽድቃ ተግባራዊ ማድረጓ በአህጉሪቱ ያለውን የገበያ ፍላጎት እንድትጠቀም አስችሏታል፡፡
የምርት ቁጥጥርና ክትትል፡ በህገ-ወጥ የምርት ክምችትና በህገ-ወጥ ኬላዎች ላይ የተደረገው ጥብቅ ቁጥጥር ምርቶች ወደ ውጭ ገበያ እንዲወጡ መንገድ ከፍቷል፡፡
የዋጋ ተመን ክለሳ፡ የማነጻጸሪያ ዋጋ ተመን በየወቅቱ ከዓለም አቀፍ የገበያ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ እንዲከለስ መደረጉ መሆኑ ተነስቷል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ መሻሻል፡ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር አገልግሎት በስፋት ስራ መጀመሩና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለው የምድር ትራንስፖርት አመቺ መሆን የሎጂስቲክስ ወጪን በመቀነስ ለንግዱ መሳለጥ ትልቅ እገዛ ማድረጉን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በምርትና ምርታማነት ላይ ያመጣው መነቃቃት ሀገሪቱ ከውጭ ንግድ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲያድግና የንግድ ሚዛኗ እንዲሻሻል መሰረት መጣሉ ተመላክቷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.