የተስፋ ብርሃን ፈንጣቂ የገብረክርስቶስ ሥንኞች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ዘመን ቀመር የነሐሴ ወር የመጨረሻ ሳምንት ላይ እንገኛለን፤ ክረምቱ ወደ ፍጻሜው እያመራ፣ ተፈጥሮ ራሷን ለአዲሱ ዓመት ስታዘጋጅ የምንታዘብበት ወቅት ነው።
በዚህ የሽግግር ሰዓት ላይ ሆነን የሠዓሊና ገጣሚ ገብረክርስቶስ ደስታን “አንተ ነህ መስከረም” የተሰኘውን ግጥም ብንመረምር፤ ወቅቱ ለምን ለኢትዮጵያውያን ልዩ ትርጉም እንደሚይዝ በጥልቀት እንረዳለን።
ግጥሙ የተፈጥሮን ውበት ብቻ ሳይሆን የሰው ልብ መነቃቃትን፣ የዘመን መለወጥን እና አዲስ ተስፋን በሚያስደንቅ ሥዕላዊ ቋንቋ ይቀርፃል።
ግጥሙ ሲጀምር ሰማይንና ምድርን በሠዓሊ ዓይኑ በቃላት ብሩሹ ይስላል።
«አንተ ነህ መስከረም፣
የሐምሌን ጨለማ የነሐሴን ዝናም፣
የሻርከው አንተ ነህ፣ በብርሃን ውበትህ…
የሐምሌና የነሐሴ ግራጫማ ዝናብና የደመናው ክብደት ያስከተለውን ድንግዝግዝታ የሚገፍፈው መስከረም እንደሆነ በሥንኞቹ ይነግረናል፤ ብርሃኑ ራሱ የክረምቱን ሐዘን አጥቦ አዲስ ውበትን የሚያላብስ ኃይል ሆኖ ይሳላል።
ከሰማይ ማዶ የሚታየው ቀስተ ደመና፣ በሜዳው ላይ የተነጠፉት ቢጫና ነጭ አበቦች፣ የክረምቱን ከባድ ሸክም አቅልለው መልክአ ምድሩን ወደ ፀሐያማና ብሩህ ገጽታ የሚቀይሩ ምልክቶች ናቸው።
ግጥሙ ይቀጥላል…
በክረምቱ ወራት ሰማዩን ያስጌጠው፣
የማርያም መቀነት በቀለም ያበደው፡፡
ጤዛው አርሶታል መሬቱ ላይ ለቆ፣
በቀይና ቢጫ መስኩ ተለቅልቆ፡፡
መስከረም የፍጥረት መታደስ ወር ነው።
ገጣሚው የተፈጥሮን ሕይወት ከሰው ልጅ እንቅስቃሴ ጋር በማዋሐድ ሰፊና ሕያው ሥዕል ይፈጥራል። ለዚህ ጥበቡ ሠዓሊነቱ ሳይጠቅመው አልቀረም።
ከስደት የተመለሱ ወፎች ጎጇቸውን እንደገና ይሠራሉ፤ ንቦች በአበባ መካከል ይርመሰመሳሉ፤ አራዊትና ግልገሎቻቸው በመስክ ላይ ይፈነጥዛሉ።
ዛፎች የሚተነፍሱ ያህል ንፋሱ የአገሩን ጣዕመ ሽታ ተሸክሞ ይነፍሳል፤ ሕፃናት በሜዳው ላይ እየሮጡ ሳቅና ጨዋታቸውን ያስተጋባሉ።
ይህ ሁሉ የተፈጥሮና የሰው ልጅ ትስስር የዘመኑን መታደስ ያበስራል፤ የክረምት ብቸኝነት በጋራ ደስታ ይተካል።
በሽቱ መዓዛህ ለውጠው ዓመቱን፣
ይታደስ ያረጀው ፍጥረት ሌላ ይሁን፡፡
ከምረው ዘመኑን ካበው ባመት ባመት፣
በወሩ ደረጃ ፍጥረት ይጓዝበት፡፡
ፍየሎች ይዝለሉ ቅጠል ይበጥሱ፣
ከተሰደዱበት ወፎች ይመለሱ፡፡
ግጥሙ ወደ ማጠቃለያው ሲደርስ መስከረም ከባህላዊ መገለጫዎች ጋር ይዋሐዳል።
የአደይ አበባ ማብቀል፣ የመስቀል ደመራ ችቦ፣ በበረዶ ንጽህና የሚመሰለው ነጭ የባህል ልብስ፣ የቡቃያና የእሸት መዓዛ… እነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያን መስከረም ከየትኛውም ወቅት የተለየ ያደርጉታል።
ገጣሚው ይህን ብዙ ገጽታ ያለው ውበት በደመቀ ቃላት ይገልጻል፤ ሐዘንን የሚያርቅ የገነት ምሳሌ አድርጎ ይሥለዋል፣ መስከረምን።
የዘመን መለወጫው ደስታ በወለላ ማርና በጠጅ ጣዕም፣ በዘፈንና በዕልልታ ይደምቃል፤ ሕዝቡ ለሰላም፣ ለሥራ ፍሬና ለተፈጥሮ ውበት የክብር ውዳሴ ያቀርባል።
የደስደስ ያሰሙ ንቦች ይራኮቱ፣
ይንጠራሩ አበቦች ይንቁ ይከፈቱ፡፡
አንበሳና ግልገል በመስኩ ይፈንጩ፣
ከብቶች ሣሩን ይንጩ፡፡
ሕፃናት ይሩጡ ይሳቁ ይንጫጩ፣
ዛፎች ይተንፍሱ፣ የነፋሱ ጠረን፣
ይሰራጭ በቦታው ያውደው አገሩን፡፡
ገብረክርስቶስ ደስታ በ«አንተ ነህ መስከረም» ግጥሙ፣ ጊዜ ከክረምት ወደ ብራ ሲሸጋገር የሚፈጠረውን የሐሳብና የስሜት ትንሣኤ በሕያውነት ያሳየናል።
መስከረም የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን የሐዘን ማብቂያ፣ የተስፋ መጀመሪያ እና የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ጋር ተዋህዶ አዲስ ምዕራፍ የሚጀምርበት ወር መሆኑን በአንጸባራቂ ቀለማት ይነግረናል።
ዛሬ፣ የነሐሴ ወር ወደ ፍጻሜው ሲቃረብ፣ ይህ የተስፋና የትንሣኤ መንፈስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በቅርበት ይሰማናል፣ አዲሱ ዓመት በራፍ ላይ ነውና፡፡
በአፈወርቅ እያዩ