Fana: At a Speed of Life!

‎የ “4ጂ” ተጠቃሚ ከተሞችን ቁጥር ወደ 1 ሺህ 500 ለማሳደግ ይሰራል – ፍሬህይወት ታምሩ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የ “4ጂ” ተጠቃሚ ከተሞችን ቁጥር ወደ 1 ሺህ 500 ለማሳደግ ይሰራል አሉ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ
ኢትዮ ቴሌኮም “የቀጣዩ አድማስ”የ3 ዓመት ስትራቴጂ 2ኛ ዓመት የስራ ዕቅድ ይፋ አድርጓል።
ዕቅዱ የደንበኞችን ቁጥር ከማሳደግ ባሻገር የኔትወርክና የአገልግሎት ጥራትን ማሳደግ ዋነኛ ግቡ ማድረጉን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ አብራርተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ከዚህ ቀደም የነበሩትን ከ90 ሚሊየን በላይ የደንበኞች ቁጥር ወደ 92 ነጥብ 3 ሚሊየን ለማሳደግ ዉጥን እንደተያዘ እና ይህንን የአገልግሎት ጥራት ማሳደግ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ ተናግረዋል፡፡
የ4ጂ ተጠቃሚ ከተሞችን ቁጥር ከ1 ሺህ 200 ወደ 1 ሺህ 500 ለማሳደግ እንዲሁም የ5ጂ ተጠቃሚ ከተሞችን ቁጥር ከ33 ከተሞች ወደ 73 ለማሳደግ መታቀዱንም አስረድተዋል።
ከ60 ሚሊየን በላይ የነበረዉን የቴሌብር የደንበኞች ቁጥር ከ67 ሚሊየን በላይ ለማሳደግ ግብ እንደተያዘም አመልክተዋል።
ተቋሙ የሚያገኘውን ገቢ ከስልክ ግንኙነት ባሻገር ከ312 በላይ በሆኑ የተለያዩ የቴሌኮም ምርትና አገልግሎቶች 295 ቢሊየን ገቢ ለማግኘት ማቀዱን እና ከዚህ ዉስጥም በዉጭ ምንዛሪ 253 ሚሊየን ዶላር ለመሰብሰብ ዉጥን መያዙን ጠቁመዋል፡፡
የኔትወርክ ተጠቃሚ ያልነበሩ 1ሺህ 400 የገጠር ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ማድረግ የሚለውም በዕቅዱ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል መሆኑን አንስተዋል።
ስትራቴጂው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ዕዉን በማድረግ ሰዉ ተኮር ተግባራትን ማዕከል ያደረገ እንደሆነም ተመላክቷል።
በአመለወርቅ መኳንንት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.