Fana: At a Speed of Life!

የጉባ ብሥራት ርዕይ መገለጫ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ አጠቃላይ የልማት ምዕራፍ ውስጥ የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት እና የኑሮ ውድነትን ማቃለል የሁልጊዜ የመደመር መንግሥት ቀዳሚ ትኩረት ሆኖ ቆይቷል።

ከዚህ አንፃር መንግሥት ኢትዮጵያን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ከፍታ ለማሸጋገር ካቀዳቸው የጉባ ብሥራት የሆኑት የ30 ቢሊዮን ዶላር ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው።

ባለፈው ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዕለቱም መንግሥት በቤቶች ልማት፣ በመሠረተ ልማትና በኢኮኖሚ አቅጣጫዎች ላይ ያስቀመጣቸው ግቦችና የተከናወኑ ተግባራት የዕድገቱን አቅጣጫ በግልጽ ያሳዩ ነበሩ።

በመድረኩ ላይ ከ1 ሚሊዮን በላይ ቤቶች እንደሚገነቡ በጉባ ብሥራት መልክ ተገልጾ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለፉት 7 ዓመታት ብቻ እንደ ሀገር 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቤቶች መገንባታቸውን አስረድተዋል።

ታዲያ ይህ አፈጻጸም ከታቀደው በላይ የተሳካ መሆኑን የሚያሳይ እና የዜጎችን የቤት ባለቤትነት ጥያቄ ለመመለስ የተደረገው ጥረት ቁልፍ ማሳያ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀጣዮቹ 5 ዓመታት ውስጥ ከጉባ ብሥራት ግዙፍ ዕቅዶች መካከል አንዱ በሆነው የቤቶች ልማት ዘርፍ ቢያንስ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት ርዕይ መያዙንም በወቅቱ ተናግረው ነበር።

አክለውም ይህንን ግብ ለማሳካት ጠንካራ ፖሊሲዎች ተቀርጸው እየተሠሩበት እንደሆነና ከዚህም አልፎ እንደ ስሪ ዲ (3D) ቴክኖሎጂ ያሉ ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን በወቅቱ አብራርተዋል።

ከንድፈ ሐሳብ ወደ ተጨባጭ ተግባር መሸጋገርን መርህ ያደረገው የመደመር መንግሥት፣ የጉባ ብሥራቶቹን ትርጉም በተግባር እያረጋገጠ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መዋቅራዊ ርምጃ መውሰዱን በዛሬው ዕለት አብስሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም ስምምነት ላይ መደረሱን ይፋ አድርገዋል።

ይህ ተቋም በተለይ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የረጅም ጊዜ የቤት መግዣ ፋይናንስ እጥረት እንዳያጋጥማቸው በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

ከጉባ ብሥራት ርዕይ ጋር ተያይዞ ሲታይ ይህ ርምጃ መንግሥት የገባውን ቃል በባንክና በፋይናንስ ሥርዓት ጭምር በመደገፍ በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን አመላካች ነው።

ባለፉት ዓመታት የታዩት የቤቶች ልማት ስኬቶች፣ አሁን ላይ እየተተገበሩ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች፣ እንዲሁም የቤት መግዣ ብድር ማጠናከሪያ ኩባንያ መቋቋም፤ መንግሥት የገባውን ቃል በመሬት ላይ ባሉ ተጨባጭ ውጤቶች እየፈጸመ መሆኑን በግልጽ ያሳያሉ።

በዘላቂነት የሚታዩት እነዚህ የልማት እርምጃዎች የኢትዮጵያን የነገ ዕድገት አስተማማኝ መሠረት የሚጥሉ ናቸው።

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.