Fana: At a Speed of Life!

በዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ምደባ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ሊዘረጋ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዩኒቨርሲቲዎች ከተማሪዎች ምደባና ዝውውር ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከቀጣዩ የትምህርት ዘመን ጀምሮ በቴክኖሎጂ የታገዘ አዲስ የአሰራር ሥርዓት ይዘረጋል አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)፡፡

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ዩኒቨርሲቲዎች የሙያና የሥነ ምግባር እሴቶች የሚገነቡባቸው የአካዳሚክና የምርምር ተቋማት ናቸው፡፡

የሕብረተሰቡ የሞራልና የእውቀት መሪዎች በመሆናቸው የሙያ ሥነ ምግባርንና የሞራል እሴቶችን በመላበስ ማህበረሰቡን በእውቀትና በሙያ ሊደግፉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ስብጥር ብዝሃነትን ባካተተ፣ መተዋወቅን፣ መከባበርን፣ መቻቻልንና ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዩኒቨርሲቲዎች ከተማሪዎች ምደባና ዝውውር ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከቀጣዩ የትምህርት ዘመን ጀምሮ በትምህርት ሚኒስቴር በቴክኖሎጂ የታገዘ አዲስ የአሰራር ሥርዓት እንደሚዘረጋ ገልጸዋል።

ከበጀት አጠቃቀም ረገድም ተቋማቱ የተመደበላቸውን በጀት ለታቀደለት ዓላማ ብቻ በቁጠባና በተጠያቂነት መንፈስ ማዋል እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ዩኒቨርሲቲዎች ሀገርን የሚያሻግሩ የእውቀት ማዕከላት ሊሆኑ እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.