የአፍሪካ ኅብረት እና አሜሪካ ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ኅብረት እና አሜሪካ ያላቸውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሞሐመድ አሊ ዩሱፍ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ፍራንክ ጋርሲያን ተወያይተዋል።
ውይይቱ በአፍሪካ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነት ለማደስ እና አህጉራዊ በሆኑ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ ለመለዋወጥ ያስቻለ እንሆነ ተገልጿል።
ሊቀመንበር ሞሐመድ አሊ ዩሱፍ በውይይቱ የሁለቱን ወገኖች ታሪካዊ ግንኙነት በማንሳት፣ በቀጣይም በኅብረቱ አባል ሀገራት እና በአሜሪካ መካከል የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ትብብርን ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የአሜሪካው የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ፍራንክ ጋርሲያ በበኩላቸው፣ አሜሪካ አፍሪካን ቅድሚያ ትኩረት የምትሰጥባት አህጉር መሆኗን ገልጸው፤ አስተዳደራቸው ከህብረቱ እና ከአባል ሀገራት ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ በቅርበት ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ወገኖች በ«አፍሪካ ህብረት እና አሜሪካ ስትራቴጂክ የኢንቨስትመንት የስራ ቡድን» ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኙ የትኩረት አቅጣጫዎችንም ገምግመዋል።
በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በሰላም እና ደህንነት፣ በዲፕሎማሲ እንዲሁም በመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ያለውን ትብብር ማሳደግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የተገቡ ቃልኪዳኖችን ወደ ተጨባጭ እና ለሁለቱም ወገን ጠቃሚ ወደሆኑ ውጤቶች መቀየር አስፈላጊ መሆኑን በመስማማት ስትራቴጂካዊ ግንኙነቱን ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በእመቤት ሲሳይ