Fana: At a Speed of Life!

የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ ለኢትዮጵያ ተደማሪ አቅም የሚሰጥ ነው – የግድቡ ጎብኚዎች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ ለኢትዮጵያ ተደማሪ አቅም የሚሰጥና ለትውልድ የሚሻገር ቅርስ ነው አሉ ግድቡን የጎበኙ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች መካከል አቋርጦ በሚሄደው የኦሞ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለው የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግድብ ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ነው።

የግድቡ ግንባታ በአሁኑ ሰዓት ከ77 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፣ በ2021 ዓ.ም. ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የኃይል ማመንጫ ግድቡን በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስተባባሪነት የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ጎብኝተውታል።

በዚሁ ወቅት ጎብኚዎቹ የኮይሻ ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ ትልቅ ተስፋ እንደሰጣቸውና ሲጠናቀቅም ለሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደማሪ አቅም የሚፈጥርና ለትውልድ የሚሻገር ቅርስ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ግድቡ በአጭር ጊዜ ውስጥ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱም በቶሎ ለማጠናቀቅ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል ብለዋል።

ጎብኚዎቹ ኢትዮጵያ ያሏትን የውኃ ሀብቶች በመጠቀም ረገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያሳየችው ተነሳሽነት ሀገሪቱን በትክክልም «የአፍሪካ ኃይል ማማ» ያደርጋታል ሲሉም ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ግድብ በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ 24 ሰዓት እየተሠራ መሆኑን ነው ያሉት ደግሞ የግድቡ ሥራ አስኪያጅ መብራቱ ተሾመ (ኢ/ር) ናቸው።

ግድቡ 201 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን አሁን ላይ 140 ሜትር ከፍታ ላይ መድረሱን ጠቁመዋል።

ግድቡ ተጠናቆ ውኃ ሲይዝ እስከ 130 ኪሎ ሜትር ወደ ኋላ የሚተኛ ውኃ ይኖረዋል፣ በአጠቃላይ በስድስት ተርባይኖች 1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።

በታሪኩ ለገሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.