Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያውያን የተስፋ፣ የፍካትና የአብሮነት አዲስ ምዕራፍ – መስከረም

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር መስከረም የወራት መጀመሪያ ብቻ አይደለም፤ የተፈጥሮ መታደስ፣ የሕይወት አዲስ ጅማሮና የነፍስ መረጋጋት ምሳሌም ጭምር ነው።
የክረምቱ ከባድ ደመና፣ ጭጋግና የዝናብ ወጀብ አልፎ ሰማዩ ጥራት የሚያገኝበት፣ ምድርም በአደይ አበባና በደማቅ ሐመልማል አጊጣ ሰዎችን በደስታ የምትቀበልበት የብርሃን ወር ነው።
በዚህ ወቅት ተፈጥሮ ብቻ ሳትሆን የሰው ልጅ አዕምሮና መንፈስም አሮጌውንና አሰልቺውን የጭንቅ ጊዜ አራግፎ በአዲስ ተስፋ ይሞላል።
መስከረም የድካም ፍሬ የሚታይበት፣ የረሃብና የጭንቀት ስጋት ተወግዶ የበረከትና የምርት ዘመን መቃረቡ የሚበሰርበት ወር ነው።
በየሜዳውና በየጎዳናው የሚፈኩት ቢጫ አደይ አበቦችና የምድር ልምላሜ ለሰው ልጅ ሕሊና ትልቅ እርካታን ይፈጥራሉ።
የደፈረሱ ወንዞች ኩልል ብለው የሚጠሩበት፣ ወፎች በደስታ የሚዘምሩበትና አየር በነፃነት የሚነፍስበት ወቅት በመሆኑ፤ በሐዘን ላይ ያሉ ቤተሰቦች እንኳን ሳይቀሩ ከሐዘናቸው ወጥተው የአዲስ ቀን ብርሃንን የሚያዩበት የፈውስ ጊዜ ነው።
ወሩ የበርካታ ታላላቅ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላት መገኛ በመሆኑ በሕዝቦች ዘንድ ልዩ ስፍራ አለው፡፡
አዲስ ዓመት (እንቁጣጣሽ) ህጻናት “አበባ አየሽ ወይ” እያሉ አዲሱን ወርና ዓመት በፍቅርና በምኞት የሚቀበሉበት የአዲስ መንገድ ጅማሮ ነው።
የመስቀል በዓል – የደመራ በዓል ተከብሮ የብርሃንና የእምነት ማሳያ ሆኖ የሚያገለግልበት ነው።
የእምነቱ ተከታዮች ፍቅሩን በመስቀል ላይ የገለጸላቸውን አምላካቸውን በማሰብ የሚያከብሩት ይህ በዓል፤ ፍቅር የሚጎለብትበትና አንዱ ለአንዱ መተሳሰቡ ከፍ የሚልበት በመሆኑ ማህበራዊ አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው።
ኢሬቻ – የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት የሕይወት፣ የሰላምና የምስጋና በዓል ነው። በዚህ በዓል የተጣሉት የሚታረቁበት፣ ይቅር ለአምላክ ብለው ፍቅራቸውን የሚያድሱበትና መተሳሰባቸው የሚጎለብትበት ነው።
ጊፋታ – ጊፋታ የወላይታ ሕዝብ የዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን፤ ልክ እንደ ሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት ሁሉ የመተሳሰብና የመተባበር እሴቶች ጎልተው ይታዩበታል።
የመስከረም ሌላኛው ትልቅ እሴቱ ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከሩ ነው፡፡
ተጠፋፍተው የቆዩ ቤተሰቦችና ጎረቤቶች የሚጠራሩበት፣ ተጣልተው የከረሙ የሚታረቁበት፣ የተራራቁ የሚገናኙበትና የመረዳዳት ባህል ይበልጥ የሚጎለብትበት እንደመሆኑ ማህበራዊ ህይወትን ያጠብቀዋል።
ህጻናት በየቤቱ እየዞሩ አበባና የመልካም ምኞት መግለጫ ሲያድሉ፤ አዋቂዎች ደግሞ ተሰብስበው በፍቅር ማዕድ ሲካፈሉ የአብሮነት እሳቤው ይበልጥ ይጠናከራል።
ኢትዮጵያ አሮጌውን ዓመት ሸኝታ አዲሱን ዓመት ልትቀበል ጥቂት ቀናት ብቻ በቀሩበት በዚህ ወቅት፤ መስከረም ይዞት የሚመጣው ተስፋ ለሀገሪቱ ሰላም፣ ለሕዝቦቿ አንድነትና ለተሻለ እድገት ትልቅ ብርሃን ሆኖ ይናፈቃል።
መስከረም የቆየውን አራግፎ አዲሱን በበጎ መንፈስ የመቀበያ የኢትዮጵያዊያን ዘላቂ የሕይወት ምዕራፍ ነው።
በታሪኩ ለገሰ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.