የአርቲስት እልፍነሽ ቀኖ አስከሬን ሽኝት መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንጋፋዋ አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ አስከሬን ሽኝት መርሐ ግብር በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል።
በአፋን ኦሮሞ የሙዚቃ ሥራዎቿ የምትታወቀው አንጋፋዋ አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ ጳጉሜን 1 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷ ይታወሳል።
የአርቲስት እልፍነሽ ቀኖ የቀብር ሥነ ሥርዓትም በአምቦ ከተማ የሚፈጸም ይሆናል።
ተወዳጇ አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ ለበርካታ ዓመታት በተለይም በትግል ዘፈኖቿና በግጥሞቿ ለኦሮሞ ሕዝብ መብት ስትታገል ቆይታለች።
አርቲስቷ የጥበብን ኃይል በመጠቀም በሕዝባዊ ትግል ውስጥ ከፍተኛ ሚና በመጫወት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ድምጻውያን መካከል ትጠቀሳለች።
የኦሮሞ ሴቶች የጀግንነትና የጽናት ምልክት የሆነችው እልፍነሽ ቀኖ÷ በምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው “ሲቡ ጉቶ” በተባለች ስፍራ በ1954 ዓ.ም ነበር የተወለደችው።
አርቲስት እልፍነሽ በ1969 ዓ.ም ወደ ትግል በመቀላቀል ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሥነ ጥበብ ሥራዎቿ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስታበረክት ቆይታለች።
አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ የሁለት ሴት ልጆች እናት ነበረች።