ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመው የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም አቀፍ የጂኦ ፖለቲካ ምህዳር የኃይል ሚዛን እየተቀየረ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገንና የሁለትዮሽ ጥምረቶችን በማካሄድ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እየሰራች ነው፡፡
ኢትዮጵያ የብሪክስ አባልነቷን በመከተል የተለያዩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባሕር በር ለኢትዮጵያ ወሳኝ የኢኮኖሚ ጉዳይ መሆኑን በ18ኛው የብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ላይ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
ይህ የብሪክስ ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት በራሳቸው የመወሰን አቅማቸውን የሚያሳድግ ከመሆኑ ባሻገር፤ ኢትዮጵያ ለምትከተለው የራስን ችግር በራስ መፍትሔ የመስጠት እንዲሁም የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ጋር የሚሄድ ነው፡፡
ባለብዙ ዋልታ ሥርዓትና ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም ያላቸው ኃያላን ሀገራት እየበረከቱ ባሉበት በዚህ ወቅት የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስቀደም ከተለያዩ ሀገራት ጋር መስራት አስፈላጊ ነው፡፡
ብሪክስ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖን ለማስፋት ከአካባቢያዊ ጥምረት ባሻገር የሚደረግ ዓለም አቀፋዊ አንድምታ ያለው ጥምረት ነው፡፡ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ለጋራ ልማትና ደህንነት ለመስራት የሚችሉበትን መንገድም ፈጥሯል፡፡
ይህ መድረክ የኢትዮጵያና ኢራን የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ድጋፍ ያገኘበት፣ ለዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ምክር ቤት የአፍሪካ ብቸኛ እጩነት ቅቡል የሆነበት እንዲሁም ለኢትዮጵያ የኮፕ 32 አዘጋጅነት ድጋፍ የተሰጠበት ነበር፡፡
የባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ላይ የምትሳተፈው ኢትዮጵያ በብሪክስ ጉባዔ ላይ የተፈጠሩትን ዕድሎች በመጠቀም የተለያዩ የሁለትዮሽ ውይይቶችን አድርጋለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በብሪክስ ጉባዔ ለመካፈል በተገኙበት ወቅት ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ከአቡ ዳቢ አልጋ ወራሽ ልዑል ሼህ ኻሊድ ቢን ሙሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያ፣ ከማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም፣ ከኢራን ፕሬዚዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን እንዲሁም ከህንድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡
ይህም ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አክብረው በጋራ ሊሰሩ ከሚችሉ ሀገራት ጋር በጋራ ለመስራት የተገኙ እድልና አጋጣሚዎችን በአግባቡ እንደምትጠቀም የሚያሳይ ነው፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ እየሄደች ያለችበትን የተጽዕኖ ፈጣሪነትና የከፍታ መንገድ በተጨባጭ የሚያመላክት ነው፡፡
በቤተልሔም ግርማ