Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ፥ በቀይ ባህር የተደቀነውን ስጋት ለመመከት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ቀጣናውን ከሽብርተኝነትና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች በመከላከል ረገድ ለዘመናት ሰፊ ልምድ አካብታለች፤ ጠንካራ ወታደራዊ አቅምም መገንባት ችላለች፡፡
ይህንን አቅሟንና ልምዷን ለዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ወሳኝ መተላለፊያ ለሆነው የቀይ ባህር ቀጣና ሰላምና ደህንነት ለማዋል ደግሞ የባህር በር ማግኘት ቁልፍ ርምጃ ነው፡፡
በቅርቡ እየተዘገበ እንደሚገኘው፤ የየመን ሁቲ አማፂያን በቀይ ባህር እና የባብ ኤል ማንዳብ ወሳኝ ቦታዎች እያደረጉት ያለው ሰሞነኛ እንቅስቃሴ የቀይ ባህር ቀጣና ደህንነትና የመርከቦች እንቅስቃሴ ስጋት መደቀኑ ተነግሯል፡፡
ታጣቂ ቡድኑ ከሳኡዲ ዓረቢያ መንግሥት ጋር የገባበትን ግጭት ተከትሎ በቀይ ባህር በሚንቀሳቀሱ የሀገሪቱ መርከቦች ላይ ጥቃት ሲፈፅም የቆየ ሲሆን፤ ሪያድም በቡድኑ ላይ የአፀፋ ርምጃዎች ስትወስድ ቆይታለች፡፡
በኢራን እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው ሁቲዎች ባለፉት ሳምንታት በቀይ ባህር ባደረጉት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ የንግድ መስመሮችን መቆጣጠራቸውም ነው የተገለጸው፡፡
በተለይም በቀይ ባህር ከአሰብ ወደብ በ64 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የሞካ ወደብ ስትራቴጂያዊ አካባቢ መቆጣጠራቸው በቀጣናው ደህንነትና በዓለም መርከቦች እንቅስቃሴ ላይ አደጋ ደቅኗል፡፡
በተጨማሪም የየመን ምዕራባዊ የባህር ዳርቻ አካባቢዎች ማለትም የባብ ኤል ማንዳብ መተላለፊያ፣ ፕሪምና ሃኒሽ የተባሉ የቀይ ባህር አካባቢ ደሴቶችን ተቆጣጥረዋል፡፡
የቡድኑ ሰሞነኛ እንቅስቃሴ ተከትሎ በአካባቢው የሚተላለፉ መርከቦች ቁጥር ከ50 ወደ 28 ዝቅ ማለቱን ዓለም አቀፉ የንግድ ደህንነት ተቋም ኬፕለርን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በዚህም የዓለም የነዳጅ ዋጋ መጨመሩንና በቀይ ባህር ተጋሪ ሀገራት እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ የደህንነት ስጋትና የኢኮኖሚ ጫናን እያስከተለ ይገኛል፡፡
ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ያነሳችው የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለራሷም ሆነ ለቀጣናው ሀገራት ሰላምና ደህንነት ወሳኝ የሚሆነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በአንድ ቃለምልልስ ወቅት እንዳሉት፤ የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ዓለምን እንደፈተነው ሁሉ ቀይ ባህር የደህንነት አደጋ ቢገጠመው የመጀመሪያዋ ተጎጂ ኢትዮጵያ ናት፡፡
በቀይ ባህርና በኤደን ባህር ሰላጤ የሚከሰቱ የደህንነት ችግሮች በምስራቅ አፍሪካ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንደሚፈጥሩ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ጎረቤቶቻችን ይህን ተረድተው ለኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ምላሽ ሊሰጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡
የቀይ ባህር ተጋሪ ሀገራት በአካባቢው ከፍተኛ የደህንነት ስጋትና የንግድ መስመሮች መስተጓጎል መኖሩን እየተመለከቱ እንኳን ችግሩን እንዴት እንካለከለው በሚለው ጉዳይ ላይ ከስምምነት አለመድረሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ካላገኘች ኢኮኖሚዋ አያድግም ብቻ ሳይሆን፤ ቀጣናዊ ኢኮኖሚ ትስስርና የጋራ እድገት ሊረጋገጥ እንደማይችልም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የቀይ ባህር ደህንነት እንዲጠበቅና የመርከቦች ደህንነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም የባህር ላይ ውንብድናንና ሽብርተኝነትን አስቀድሞ መከላከል ይቻል ዘንድ፤ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና ጸጥታን ለማረጋገጥ፣ ድንበር ዘለል ሽብርተኝነትን ለመከላከልና በሕግ ማዕቀፍ ለመቆጣጠር የቆየ ሰፊ ልምድ አላት።
በዚህም የአፍሪካ ህብረትና ቀጣናዊ የደህንነት ትብብሮችን በመጠቀም ከቀጣናው ሀገራት ጋር በቅንጅት እየሰራች ሲሆን፤ በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ሚናዋን አጠናክራ ቀጥላለች፡፡
የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት ማረጋገጥ መሰል የሽብር ጥቃቶችን በመመከት የዓለም የንግድ እንቅስቃሴን ለማሳለጥ የሚያስችል የደህንነት ዋስትና ይፈጥራል፡፡
በሚኪያስ አየለ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.