የትምህርት ማቋረጥ ምጣኔን የቀነሰ ታሪካዊ ርምጃ – የት/ቤት ምገባ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ልጆች የሚመገቡት በቂ ምግብ ማግኘት አለመቻላቸው በትምህርት ገበታ ላይ እንዳይገኙ፣ የተገኙትም በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡
ይህም ልጆችን ለረሃብ ከመዳረግ ባለፈ ለተለያዩ የአዕምሮ መንፈስ ጭንቀቶች የሚዳርግ እንዲሁም ትምህርት የመቀበል አቅማቸው በመቀነስ ብቁ ትውልድ የመፍጠር ጉዞ ላይ ተግዳሮት የሚሆን ነበር፡፡
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ልጆች በቂ ምግብን ማግኘት ባለመቻላቸው ብቻ ለበርካታ የጤና እክሎች ይዳረጋሉ፡፡
ለአብነትም በቂና የተመጣጠነ ምግብን የማይመገቡ ልጆች ለበሽታ ተጋላጭነታቸው ይጨምራል፤ በዚህ የተነሳም የትምህርት ገበታቸው ላይ ለመገኘት ይቸገራሉ፡፡
በተጨማሪም ከእኩዮቻቸው በመለየታቸው በሚደርስባቸው መገለል የተነሳ በሚሰማቸው የበታችነት ስሜትና አካባቢያቸው ላይ በሚያዩት ሁኔታ የተነሳ ለከፍተኛ ጭንቀትና ድብርት ይጋለጣሉ፤ ይህን ተከትሎም ከትምህርት ገበታቸው ለመቅረት ይገደዳሉ፡፡
ሌላውና መሠረታዊው ችግር ደግሞ ትኩረት መሰብሰብና ትምህርትን በአግባቡ ለመከታተልና ለመረዳት ችግር በመፍጠሩ የተነሳ በርካታ ተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ ዝቅተኛ አድርጎት ነበር፡፡
ዛሬስ? አሁን ላይ ይህ ታሪክ ሆኗል፡፡ ተማሪዎች ይህን ሁሉ ችግር እየተጋፈጡ ትምህርታቸውን በአግባቡ መቀጠልና ተገቢ ውጤት ማምጣት እንደማይችሉ የተረዳው የመደመር መንግሥት የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራምን አስጀምሯል፡፡
በመንግሥት፣ በሌሎች በጎ አድራጎትና የልማት አጋር ድርጅቶች ትብብር የሚካሄደው ይህ የተማሪዎች ምገባ እናቶች ለልጆቻቸው ያለስስት እንደሚያዘጋጁት፣ ልጆችም ከእናቶቻቸው እጅ ያለሰቀቀን ወስደው እንደሚመገቡት ዓይነት የቤተሰባዊነት መልክ አለው፡፡
የምግብ አቅርቦት መኖሩ የቤተሰብን ኢኮኖሚ ጫና የሚያቃልል እና ተማሪዎች ከስጋት ወጥተው ትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ ያስችላል፡፡
በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት በሚመጡ በሽታዎች የተነሳ የሚቀሩ ተማሪዎችን መጠን ቀንሷል፤ እንዲሁም የአቅም ልዩነትን መሠረት አድርገው ከሚፈጠሩ የሥነ ልቦና ችግሮች ተማሪዎችን ታድጓል፡፡
በሌላ በኩል የትምህርት ፍላጎታቸው እንዲጨምር፣ የመረዳት አቅማቸው እንዲያድግ ትልቅ ሚናን ተጫውቷል፤ በተጨማሪም ይህ የምገባ ሥርዓት በገጠሪቱ ክፍል ያሉ የሴት ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ በአግባቡ እንዲገኙ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ÷ የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት የተማሪዎችን ውጤት ከማሻሻሉ ባለፈ ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር እንዲቀንስ ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡
ባለፉት 5 ዓመታት በተሰራው ሥራ የተማሪዎች ምገባ አገልግሎት አቅም ማደጉን ገልጸው÷ አሁን ላይ 8 ነጥብ 9 ሚሊየን ተማሪዎች የትምህርት ቤት ምገባ ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
የት/ቤት ምገባ መርሐ ግብር የተማሪዎችን የትምህርት ማቋረጥ ምጣኔ የቀነሰ ብቻ ሳይሆን ቀድሞ ከነበረው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በማስቻል ታሪካዊ ዐሻራ ያኖረ ነው፡፡
በቤተልሔም ግርማ