Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ የእህትማማች ከተሞች ትስስርን በማስፋት ከዓለም ከተሞች ጋር ያላትን ግንኙነት እያሳደገች ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አዲስ አበባ በተለያዩ ዘርፎች የጋራ ትብብርን ለማጠናከር በምታደርገው ጥረት ባለፉት አምስት ዓመታት የከተማዋ የእህትማማች ከተሞች ትስስር ከ20 ወደ 30 ከተሞች አድጓል፡፡
አዲስ አበባ ባላት ታሪክ እና አሁን ላይ እያስመዘገበችው ባለው ሁለንተናዊ ለውጥ በርካታ የዓለም ከተሞች የእህትማማችነት ግንኙነቱን እያሳደጉ ይገኛሉ፡፡
ይህ ከከተሞች ጋር የሚኖር ስትራቴጂካዊ ግንኙነት አዲስ አበባ ከዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን ያሳድጋል፡፡
በተጨማሪም ዘመናዊ የከተማ ልማት ልምዶችን እና ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ እጅግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
የአዲስ አበባ ለውጥ ዛሬ በሁሉም መልኩ የእይታ ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል፡፡
ዓለምዓቀፍ ተቋማቶች ስብሰባዎቻቸውን አዲስ አበባ ላይ ለማድረግ ቀዳሚ ምርጫቸውን አድርገዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 221 ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ኮንፈረንሶች በአዲስ አበባ መካሄዳቸውን ከከንቲባ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
አዲስ አበባ ወደ ስማርት ሲቲ (ዘመናዊ ከተማ) ለመቀየር በምታደርገው ተከታታይ ጥረትና በምታስመዘግባቸው ስኬቶች በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችንና እውቅናዎችንም አግኝታለች።
ከእነዚህ እውቅናዎች መካከልም በሪዮዲጀነሪዮ የተቀበለችው የምገባ ኘሮግራም ሽልማት፡ በደቡብ ኮሪያ የተበረከተውና ለከተማዋ አመራር እውቅና የሰጠው የሴኡል ስማርት ከተማ ሽልማት (2024)፡ ለቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት መሻሻል በቦነስአይረስ የተሰጠው እውቅና፡ የC40 ከተሞች የብሉምበርግ ሽልማት፡ በናይሮቢ ኬንያ በተካሄደው የአፍሪካ ስማርት ከተሞች ኢንቨስትመንት ሰሚት የተሰጠው የአፍሪካ ምርጥ ስማርት ከተማ ሽልማት (2024)፡ አዲስ አበባ በመንገድ ደህንነትና ፍጥነት ማስተዳደር ላይ ባስመዘገበችው ውጤት በዓለም አቀፍ የከተሞች የዘርፉ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችባቸው ተጠቃሽ ናቸው፡፡
እነዚህ ዓለም አቀፍ እውቅናዎች የከተማዋን ሁለንተናዊ መልካም ገጽታ በዓለም መድረክ ላይ በግልጽ ያሳዩ ታላላቅ ስኬቶች ናቸው።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.