ምህረትና ዕርቅ የሀገራዊ ምክክሩ ፍሬዎች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ የምክክር መድረክ ችግሮች በሀሳብ የበላይነት የሚፈቱበትን መንገድ መጥረግ ጀምሯል።
ኢትዮጵያ ያከናወነችው ሀገራዊ ምክክር የብዙዎችን እምነት ያተረፈው፣ ውይይቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ መባቻው በጎ ፍሬዎችን በተግባር ማሳየት በመጀመሩ ነው።
ሰላምን በምኞት ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ ውሳኔዎች መገንባት ይቻላል የሚለው መርህ፣ አዲሱን ዓመት ተንተርሶ በተወሰደው ታሪካዊ የምሕረት ርምጃ አማካኝነት በተግባር ተረጋግጧል።
የመደመር መንግሥት በአዲስ ዓመት ዋዜማ በመቶዎች የሚቆጠሩ በፍርድ ቤት ውሳኔ በማረሚያ ቤት የነበሩ በይቅርታ፣ በክስ ሂደት ላይ የነበሩት ደግሞ ክሱ እንዲቋረጥ ተደርጎ በይቅርታና በምህረት ተፈትተው ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረጉ፣ በፖለቲካ ምህዳሩ ውስጥ አዲስ የምሕረትና የዕርቅ ነፋስ እንዲነፍስ አድርጓል።
ውሳኔው ጥልቅ ሀገራዊ አመክንዮና ስትራቴጂያዊ ግብ አለው። የቆዩ ቁስሎችን፣ ቂሞችንና ቅሬታዎችን ይዞ ወደ አዲስ ዘመን መሸጋገር ሀገራዊ እድገትን ያደናቅፋል።
ስለዚህ አዲሱን ዓመት በዕርቅ፣ በፍቅርና በይቅርታ በመጀመር ለዘላቂ ሰላም ምቹ ሁኔታን መፍጠር ተችሏል።
የተለያዩ የፖለቲካና የማኅበረሰብ ክፍሎች በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ላይ በተለያየ የወንጀል ድርጊት በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ እና በክስ ሂደት ላይ የሚገኙ እስረኞች በይቅርታ እና በምህረት እንዲፈቱ ላቀረቡት ጥያቄ መንግሥት ምላሽ መስጠቱ፣ ኢትዮጵያ አዲስ የእርቅና የይቅርታ ተስፋን መሰነቋን አረጋግጧል።
ይህ የተግባር ርምጃ የሚያሳየው አንድ ትልቅ እውነት አለ፤ መንግሥት ለሀገራዊ ምክክሩ ሂደትና ከእርሱም ለሚመጡ የመፍትሔ ሐሳቦች ያለውን ቁርጠኝነት ገና ከወዲሁ በተግባር ማስመስከሩን ነው።
የይቅርታውና የምህረቱ ተጠቃሚ ወገኖች አዲሱን የኢትዮጵያ ጉዞ በሰላምና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመቅረጽ ቁልፍ ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እነዚህ ወገኖች በሀገራዊ ውይይቶች ላይ በበሰለና አዎንታዊ በሆነ መንገድ በመሳተፍ፣ ለሀገራዊ መግባባት ትልቅ አስተዋጽዖ የማበርከት አጋጣሚ ተከፍቶላቸዋል።
የሰዎች አስተሳሰብ በተለያየበት፣ ፍላጎቶች በተጋጩበትና ልዩነቶች በሰፉበት ሁኔታ ውስጥ እንኳን ሳይቀር በሰላማዊ መንገድ መነጋገር፣ መከራከርና በሐሳብ የበላይነት ለመፎካከር በር ይከፍታል።
በርካታ የጦርነትና የውድመት ምዕራፎችን በማለፍ ትነሳ የነበረችው ኢትዮጵያ፤ ይህንን ታሪክ በመቀየር የሰላም፣ የሐሳብ ልህቀት፣ የምክክርና የጋራ ብልጽግና ታሪክን መሰነድ ጀምራለች።
በአጠቃላይ የምሕረት ውሳኔው ኢትዮጵያ ካሳለፈችው የፖለቲካ ውጥረትና የቂም አዙሪት ተላቅቃ ወደ አዲስ የመቻቻልና የዕርቅ ምዕራፍ እየተሸጋገረች ለመሆኗ ማረጋገጫ ነው።
ይቅርታና ውይይት የደካማነት ሳይሆን የብስለትና የአሸናፊነት ምልክቶች ናቸው። በኃይልና በመሣሪያ ሳይሆን በሐሳብ የበላይነት የምትመራ አዲስ ኢትዮጵያን ለመገንባት መሠረት የተጣለው በዚሁ የሰላም መንገድ ነው።
በመልካም ፈቃዱ