Fana: At a Speed of Life!

ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም አቅም የሚሆን ሥራ መሥራት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል- አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም አቅም የሚሆን ሥራ መሥራት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል አሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ።

‎የምሥራቅ ጎጃም ዞን የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምግማና የ2019 በጀት ዓመት የዕቅድ ትውውቅ መድረክ ተካሂዷል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ በዚህ ወቅት÷ አርቆ በማየት ነገን መመልከት፤ ዛሬ ደግሞ ለነገ መዳረሻችን አልቀን መሥራት አለብን ብለዋል።

የጋራ አላማ ላይ ለመድረስ ዕቅድ ወሳኝ ‎መሆኑን ገልጸው÷ የታቀደውን የመፈጸም አቅምን ማሳደግ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂ እንዲለማመዱና ከዕለት ፍጆታ ያለፈ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ምርት እንዲያመርቱ ዘመናዊ ግብርና ላይ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል ነው ያሉት

‎የጤና ተቋማትን፣ ት/ቤቶችን እና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለመገንባት ገቢን በአግባቡ መሰብሰብና ተቋማትን በኃላፊነት መምራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ተማሪዎች እንዲማሩ ማድረግ አለብን፤ ሰው ሳናስተምር ሀገር ማልማት አንችልም ሲሉ ማስገንዘባቸውን አሚኮ ዘግቧል።

‎ሙስና እና ሕገ ወጥነትን መከላከል እንደሚገባ ጠቅሰው÷ ለዚህም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ማስፋት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የጸጥታ ኃይሉን በማገዝ ሰላምን መጠበቅ እና ይበልጥ በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑንም አመልክተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.