ሁለቱን መሪዎች አንድ ጠረጴዛ ምን አጋራቸው?
አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) እነ ዩ ቢ ኤስ፣ ጁሊየስቤር እና ፒክቴት ተደምረው የስዊዝ ባንክ ተባሉ።
የስዊዝ ባንኮች ‘’በሌብነት የጨቀየ ገንዘብ የሚጠራቀምባቸው አግበሽባሾች ናቸው’’ ብሎ የሚያስብ ካለ ነገርን ከስሩ ያልመረመረ፤ ውሃን ከጥሩ ለመጠጣት ያልደፈረ ነው።
ስዊዘርላንድ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ዓለም በግራና በቀኝ ተከፍላ ጦር ስትጠዛጠዝ፣ ቦንብ ስትወራወርና ፈንጂ ስታፈነዳ፣ ከዛም በኋላ በቀዝቃዛው ጦርነት ቀዝቅዛ ስትደነዝዝ፤ ከግራም ከቀኝም ሳትጣበቅ በራሷ ጸንታ ቆማ የታላቅነት ምስጢርን ያሳየች ሃገር ናት።
በፋይናንስ ስርዓቷ መተማመኛ፤ በዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ ተወዳጅ ሆናም የቀጠለች ሀገር ናት ስዊዘርላንድ፡፡
ይህች ውብ ምድር ድንቅ የመስከን ሃገር ተምሳሌት ናት። ምክንያት ከተባለ፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አንዱ ጎራ የመጣበቅ አስገዳጅነት ውስጥ የመውደቅ ግዴታ ነበረባት።
ለምን? ቢባል በጦርነቱ አውድ ላይ ዋና ተዋናዮች ከነበሩት በናዚ ፓርቲ ከምትመራው ጀርመን ጋር በሰሜን፣ ከጣሊያን ጋር በደቡብ እንዲሁም ከፈረንሳይ ጋር በምዕራብ የምትዋሰን ጎረቤት ሳለች፤ ጦርነትን አምቢ አለች፡፡
ይልቁንም “ገለልተኛ ነኝ፤ ነገር ግን ለራሴ አላንስም” የሚል መርህን ተከትላ ከዛ አውዳሚ ውጥንቅጥ ውስጥ አመለጠች! እንግዲህ የስዊዝ ባንኮች የደህንነት እና የመታመን ምንጫቸው አንዱ ይኸው ነበር።
ዛሬ ስዊዘርላንድ፤ ከዙሪክ እስከ ጄኔቫ ብሎም እስከ በርን ዓለም ከተሞቿን እንደ እራሱ መኖሪያው በፍቅር የሚጠራላት የሰላም ተምሳሌት ሆና ቀረች፤ የጄኔቫ ተምሳሌት የድርድር የመግባባት የሰላም ፍኖት ሆኖ በዓለም ዜጎች ልቡና ውስጥ ታተመች፡፡
ብሄራዊ ጥቅሟን ያስጠበቀች ሃገር፤ ከግራም ከቀኝም ሰርታ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ሲሳይን አቆየች፡፡
ወደ ኒው ዴልሂ ቢዚሁ ተጉዘን፣ የአዲስ አበባን መልክ በጠራው የጄኔቫ መነፅር ለማየት ከወደድን እውነቱ ይኸው ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በኢራኑ ፕሬዚዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን ኒው ዴልሂ የውይይት ጠረጴዛ ፊት ለፊት የተቀመጠው አጀንዳ ሌላ ሊሆን አይችልም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት እንዳሉትም የአዲስ አበባ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፤ ልክ እንደ ስሟ የእንግሊዘኛው የመጀመሪያ ፊደል በ 4 ‘’A’’ የሚመራ መልክ እንዳለው ተናግረው ነበር። ACTIVE, ALTERNATIVE,ADAPTIVE,AGENDA በሚል መግለፃቸው እሙን ነው።
እስኪ ከአጀንዳ ውጭ ያሉትን 3ቱን ኤዎች (As) እንመልክት።
ይህ ወቅት የዓለም ፖለቲካ የእውር ድንብር ጉዞ ላይ ስለመሆኑ ከሞስኮ እስከ ሆርሙዝ ብሎም እስከ ቀይ ባህር ምን እየተከናወነ እንዳለ መመልከት ብቻ በቂ ነው።
በዚህ ውስጥ የነቃ ግን ደግሞ የገለልተኝነት ሚዛኑን ያልሳተ ዲፕሎማሲ መርህን መከተል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ፕሬዚዳንት መስዑድን ከበቂ በላይ ሆኖ በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ያስቀምጣል።
ወደ ሁለተኛው መርህ እንምጣ አማራጭን (ALTERNATIVE) ማብዛት፡፡ ይህ መርህ የዲፕሎማሲ እና የኢኮኖሚ አጋሮቿን በማስፋት አማራጮችን መፍጠር ላይ ያተኩራል።
በየቀጣናው ያሉ የአዲስ አበባ ወዳጆችን ማብዛት ሀገር በሆነ ስፍራ ለገጠማት መሰናክል እዛው አከባቢ ካሉ ጎረቤቶች የችግር መውጫውን መፈለግ እንደማለት ነው።
መቼም በሜዲትራንያን ባህር ላይ ለሚንሳፈፍ የኢትዮጵያ የንግድ መርከብ በችግር ጊዜ ከባህሩ 8 ሺህ ኪሎ ሜትር ከምትርቀው ከደቡብ አፍሪካ እርዳታን ከመሻት፤ 0 ኪሎ ሜትር ላይ ያለቸውን ስፔንን መጠጋት ጤናማነት ነው።
ይህ በአንድ በኩል ከመደመር መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መርህ የሚቀዳ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማረጋገጥ ከሚያስችላት ከሩቅም ሆነ ከቅርብ ሀገራት ጋር በትብብር የምትሰራ መሆኗን የሚያመለክት ነው፡፡
ይህ ደግሞ ከፕሪቶሪያ ይልቅ ማድሪድ የአዲስ አበባ ልዩ ወዳጅ ነች የሚል ትርጉም እንዳይሰጥ ሌላኛው ‘’A’’ (ADAPTIVE) ገቢር ነበብ መፍትሄ ሆኖ ይመጣል።
ከተለየ ርዕዮተ ዓለም ጥገኝነት አምልጦ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያ ጥቅም ብቻ ወግኖ መቆምን ያስቀደመ መርህ ሆኖ እንመለከተዋለን። አሁንስ የሁለቱ መሪዎች በአንድ ጠረጴዛ የመቀመጡ እንቆቅልሽ ፍቺው ተገለጠላችሁ?
የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ቁንጮዎቹ አዲስ እና ጄኔቫ ለካ ሌላም የሚጋሩት ታሪክ አለ። አጽንቶ ከዛሬ ያደረሳቸው ይህ የዲፕሎማሲ ማንነታቸው ነው።
በነቢዩ ይርጋለም