Fana: At a Speed of Life!

የአደባባይ በዓላትን በድምቀት ለማክበር የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ከወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር “የጋራ መግባባትና ስምምነት ለዘላቂ ሰላም” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ከተማ አቀፍ ኮንፈረንስ ማጠቃለያ እየተካሄደ ነው።

ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶች በተሳተፉበት በዚህ መድረክ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የፀጥታ ኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ ተስፋዬ ደንድር እንዳሉት÷ በመጪዎቹ ቀናት የሚከበሩት የአደባባይ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ በቅንጅት መስራት ይገባል።

በዓላቱ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን ጠብቀው እንዲከበሩ ሁሉም ወገን የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ብዙ ባህላዊ ቅርሶችና የተለያዩ ማንነቶች ያሏት ሀገር እንደሆነች ጠቅሰው÷ እነዚህ ብዝሃ ሀብቶች በትብብር ከተጠቀሙባቸው ለዕድገት ጠንካራ መሠረት እንደሆኑ አመልክተዋል።

ሰላም ለልማትና ለማኅበረሰብ ደህንነት መሠረት መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው÷ የፀጥታ ሥራ ቀጣይነት ያለው ትኩረት፣ ትብብር፣ መቀናጀትና የአካባቢን ሁኔታ በቅርበት መከታተልን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

በመጪዎቹ ቀናት የሚከበሩ የአደባባይ በዓላትን በድምቀት ለማክበር የወጣቶች ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ÷ ወጣቶች የበዓላቱን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶች በመጠበቅ እንዲሳተፉ ጠይቀዋል።

በተለይም የመስቀል ደመራና የእሬቻ በዓላት የሀገሪቱ ባህላዊና ማኅበራዊ እሴቶች መገለጫ በመሆናቸው በሰላምና በሥነ-ሥርዓት እንዲከበሩ የሁሉም አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

በዓላቱን ከሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻቸው ውጭ ለሌላ ዓላማ ሊያውሉ የሚችሉ ተግባራትን መከላከል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የከተማዋ ወጣቶች ለአንድነት፣ ለሰላምና ለበዓላት ስኬታማ አከባበር በባለቤትነት እንዲሳተፉም ጥሪ አቅርበዋል።

የተሳሳተ መረጃና ለሰላም የማይጠቅሙ ይዘቶች በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በህትመት እንዳይስፋፉ በጥንቃቄ መከታተል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዮናስ ጌትነት

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.