በክልሉ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የግብርና ምርትን ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ በሪሶ ፈይሳ ለፋና ዲጅታል እንዳሉት÷ የግብርና ሪፎርሙ ከኢንዱስትሪ ጋር የተሳሰረ እንዲሆን በመሥራት የግብርና ምርቶች ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት እንዲሆኑና እሴት ተጨምሮባቸው ለገበያ እንዲቀርቡ እየተሰራ ነው።
በተለይም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪያል ፓርኮችን በማቋቋም ለኢንዱስትሪዎቹ የሚያስፈልጉ የግብርና ግብዓቶችን የማቅረብ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።
በክልሉ በጥጥ፣ በቡና፣ በማር፣ በስንዴ፣ በቢራ ገብስና በበቆሎ ምርት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን ገልጸው፤ በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት በስንዴ፣ በቢራ ገብስና በበቆሎ ምርትና እሴት የመጨመር ሥራዎች በትኩረት መሰራቱን አብራርተዋል።
በምርቶች ላይ እሴት በመጨመር የተሰሩ ሥራዎች የምርት አቅምን ከማሳደግ ባለፈ፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችሉ ውጤቶችን አስገኝተዋል።
የግብርና ምርት ገበያ ማጣት ከዚህ በፊት የነበረ ተግዳሮት መሆኑን ገልጸው፤ አሁን ግን ምርትን ከገበያ ፍላጎት ጋር በማስተሳሰር እንዲመረት እና ከኢንዱስትሪዎች ጋር በማገናኘት የገበያ ሰንሰለቱን ለማጠናከር እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ ሂደት የአርሶ አደሮችን ምርት በክላስተር እንዲመረት በማድረግ፣ የቴክኖሎጂና የእውቀት ልውውጥን በማጠናከር እና የተሳካ ተሞክሮን ከአንዱ አርሶ አደር ወደ ሌላው በማስፋፋት የምርታማነት ለውጥ ለማምጣት መሠራቱን አስረድተዋል።
የክላስተር አሠራሩን ወደ ንግድ ሥራ ማሸጋገር፣ የአርሶ አደሩን ምርት ሜካናይዝድ ማድረግና የንግድ ግብርናን ማስፋፋት በቀጣይ ትኩረት ከሚሰጣቸው አቅጣጫዎች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም በ2018 ዓ.ም 1 ሺህ የሚጠጉ ትራክተሮች እንዲሁም ኮምባይነሮች መገዛታቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም አርሶ አደሩ በግብርና ምርቱ ተጠቃሚ እየሆነ ለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።
ለ2019 የበጀት ዓመት የአርሶ አደሩን አቅም በማጎልበት ግብርናን እንደ ንግድ ሥራ ለማስቀጠል ትኩረት መደረጉን ገልጸው፤ አርሶ አደሮችን በማዕከላት በማሠልጠን፣ የብቃት ማረጋገጫ በማስገኘትና በሥነ ምኅዳር እና በሚያመርቱት ሰብል መሠረት የተለየ ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
የመስኖ ልማትን ማስፋፋት፣ ሜካናይዜሽንን ማጠናከር፣ የእንስሳት እርባታንና የማር ልማትን ማሳደግ በ2019 የበጀት ዓመት በትኩረት ከሚሰራባቸው ዘርፎች መካከል መሆናቸውን ገልጸዋል።
ምርቶች በብዛት፣ በጥራትና በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑም አቅጣጫ መያዙን ጠቁመዋል።
የአርሶ አደሩን የፋይናንስ ተደራሽነት ለማሻሻልም ከፋይናንስ ተቋማትና ከባንኮች ጋር በመሥራት የአርሶ አደሩን ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ሀብት እንደ መያዣ በመጠቀም ብድር ማግኘት የሚችልበትን ሥርዓት ለማመቻቸት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ግብርና ለኢኮኖሚው እድገትና ለኢንዱስትሪ ልማት መሠረት በመሆኑ፤ ከምርት እስከ ገበያ፣ ከቴክኖሎጂ እስከ ፋይናንስ የተሳሰረ ሥርዓት በመፍጠር የአርሶ አደሩን ቀጥተኛ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዮናስ ጌትነት