የብሩህ ዘመን ማብሰሪያው ማሽቃሮ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ምድር በለምለሙ መስክ ስታጌጥ፤ ጸሐይም ከጠራው ሰማይ ስር ስትፈነጥቅ፤ ወንዞች ኩልል ብለው መፍሰስ ሲጀምሩ፤ በወርሀ መስከረም ካፊቾዎች ወደ አዲሱ ዘመን መሻገራቸውን ያበስራሉ፡፡
የካፋ ብሔር ዘመን መለወጫ “ማሽቃሬ ባሮ” ወይም ማሽቃሮ ይባላል። ማሽቃሮ ካፊቾዎች ከክረምት ጨለማ ወደ ብርሃናማው ወቅት ያሻገራቸውን፤ የተዘራውን አብቅሎ ፍሬ የሰጣቸውን አምላክ የሚያመሰግኑበት፤ በይቅርታ ልባቸውን አንጽተው የአዲሱን ዓመት አዲስ ቀን የሚቀበሉበት የዘመን መለወጫ በዓል ነው።
የማሽቃሮ በዓል መነሻው የመኸር እርሻና እና በጥንት የካፋ ገዥዎች የነበረው የግምገማ ሥርዓት እንደሆነ የብሔረሰቡን ባህልና ታሪክ አዋቂ የሆኑት አቶ ወንድሙ ማሞ ይናገራሉ።
በካፋ የመኸር እርሻ በሐምሌ ወር መግቢያ በንጉሱ አዋጅ ይጀምራል። ነሐሴ መገባደጃ ላይ በአዋጅ የተጀመረው እርሻ በአዋጅ ይጠናቀቃል።
አርሶ አደሩ እርፍና ሞፈሩን ይፈታል። ከሐምሌ አንድ ጀምሮ ካፊቾዎች ወደ አዲሱ ዘመን ለመሻገር 77 ቀናትን መቁጠር ይጀምራሉ።
የእርሻ ሥራው በንጉሱ አዋጅ ከቆመ በኋላ አጠቃላይ የዓመቱ ሥራ በንጉሱና በሚክሬቾ (ምክር ቤት) ፊት ይገመገማል።
ግምገማው ከመደረጉ በፊት ግን ‘ታቴ ክሾ’ የተባለው ቃለ አቀባይ ዓመቱን ሙሉ የሰበሰበውን መረጃ ለንጉሱ ያቀብላል ይላሉ የታሪክና ባህል አዋቂው አቶ ወንድሙ ማሞ።
በግምገማው ጥሩ የሰራ የላቀ ሹመትን ያገኛል፤ ደካማ አፈጻጸም ያሳየው ደግሞ ስልጣኑን እስከመልቀቅ የሚደርስ ርምጃ ይወሰድበታል።
የዓመቱ ስራ ተገምግሞ የቀጣዩ ዓመት ዕቅድ ከተቀመጠ በኋላ ህዝቡ ካለበት ቦታ ወደ ንጉሱ ቤተ መንግሥት ይጠራል።
ያኔ አዲሱ ዘመን ይበሰራል የካፋ ብሔር ዘመን መለወጫ ይሆናል ማለት ነው።
ይህ የካፋ ህዝቦች የስልጣኔ ማሳያ የሆነው የማሽቃሮ በዓል ካፋ ራስ ገዝ በነበረበት ዘመን እንደ ብሔራዊ በዓል በድምቀት የሚከበር፣ የፌስቲቫል ይዘት ያለው በዓል እንደነበረ ነው አቶ ወንድሙ ማሞ የገለጹት።
ማሽቃሮ ከተቋረጠ ከረጅም ዓመታት በኋላ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በየዓመቱ በመስከረም ወር በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
የማሽቃሮ በዓል አከባበር በተለያዩ ክዋኔዎች የተሞላ ነው። ዋናው የዘመን መለወጫ በዓል ከመከበሩ አንድ ቀን በፊት በዋዜማው ምሽት ፈረሰኞች በርካታ ፈረሶችን እየጋለቡ “ሞጎሾሻ” ወደተባለው ስፍራ ያመራሉ።
ሞጎሾሻ ማለት በጥንት የካፋ መንግሥት በሜንጆ ስርዎ መንግሥት ካፋን ካስተዳደሩ 19 ነገስታት የ18ቱ ነገስታት መቃብር በአንድ ስፍራ የሚገኝበት ታሪካዊ ቦታ ነው።
ፈረሰኞች ወደዚህ ስፍራ ሄደው ለነገስታቱ ክብር ሰጥተው በማግስቱ በዓሉ ወደሚከበርበት አደባባይ ይመለሳሉ።
ፈረሰኞች የነገስታቱን መቃብር ጎብኝተው ከተመለሱ እና ሀገሩ ሰላም መሆኑን ለንጉሱ ካበሰሩ በኋላ በዓሉ በሚከበርበት እለት ማለዳ የሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ያደርሳሉ።
“እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገራችሁ፤ መጪው ዘመን የተስፋ፣ የስኬት ይሁንላችሁ” ይላሉ በምርቃታቸው።
በቀድሞው የካፋ መንግሥት የነበረውን የግምገማ ሥርዓት የሚያሳይ ቲያትር ለታዳሚው የሚቀርብ ሲሆን፤ የእርድ ሥርዓትም ይከወናል።
ከዕርድ ሥርዓቱ በፊት ግን የተመረጡ ሦስት ሰንጋዎች በታዳሚው ፊት ቀርበው “ሀውቶ” በተባለ ሀረግ ይታሰራሉ።
“ሀውቶ” የተባለው ሀረግ ዘሩ የማይሞት፤ በክረምትም በበጋም የማይጠፋ፣ ተመንጥሮም ቢሆን ስሩ በራሱ ታግሎ የሚወጣ በመሆኑ ጥልቅ ትርጉም አለው።
ሀረጉ ከሰንጋው አንገትና ቀንዱ ላይ ታስሮ ይዘረጋል። ይህ ዓላማው የተጣላ እንዲታረቅ ነው ይላሉ ሌላኛው የታሪክና ባህል ተንታኙ አቶ አስራት ሃይሌ።
ማሽቃሮን ያለ ይቅርታ ማክበር አይታሰብም። የተጣሉ ካሉ ይቅር ተባብለውና እርቅ አውርደው በበዓሉ ይታደማሉ። በንጹህ ልብ ሆነው አዲሱን ዓመት ይቀበላሉ።
የተመረጡት ሰንጋዎች ከታረዱ በኋላ ሌላ እርድ ከመፈጸሙ በፊት ከታረዱት ሰንጋዎች የቅምሻ እና የጉርሻ ስርዓት ይከወናል።
እንደ አቶ አስራት ሀይሌ ገለጻ፤ “በጉርሻ ስርዓቱ ነፍሰ ጡር ሴት እንደ ሁለት ሰው ትቆጠራለች ለራሷም ለህጻኑም ተብሎ ሁለት ጊዜ ትጎርሳለች።
ማሽቃሮ ሁሉም እኩል የሚታይበት ሁሉም ደስታን የሚካፈልበት የሁሉም በዓል ነው። የማሽቃሮ በዓል መስከረም 12 ቀን 2019 ዓ.ም የሚከበር ሲሆን፤ ይህን በዓል በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስነት ለማስመዝገብ ሰፊ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡
በተስፋዬ ምሬሳ