ለአምስት ሆስፒታሎች 4 ሺህ የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ ኪቶች ድጋፍ ተደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) “በፕሮጀክት ትችላለች” ለአምስት ሆስፒታሎች 4ሺህ የማህጸን በር ካንሰር ምርመራ ኪቶች ድጋፍ ተደርጓል።
የፕሮጀክቱ የጥናት ቡድን አባል ዶ/ር ቢንያም ተፈራ እንዳሉት ፥ ፕሮጀክቱ የማህጸን በር ካንሰር ምርመራን ለማጠናከርና በኤችአይቪ እንክብካቤ ውስጥ የካንሰር ምርመራን ማዋሃድ ላይ ያተኮረ ነው፡፡
ዶ/ር ቢንያም ተፈራ በፕሮጀክቱ አማካኝነት የተበረከተው ይህ ድጋፍ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ፣በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል፤ በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣በአዳማ ሆስፒታል ህክምና ኮሌጅ እና የአሰላ ሬፈራል የማስተማሪያ ሆስፒታል የሚፈጸም ይሆናል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በዋናነት የማህጸን በር ካንሰር ቅድመ ምርመራ መነሻ ያደረገ በመሆኑ ለሆስፒታሎች የተበረከቱት 4 ሺህ ኪቶች ለዚህ የተጋለጡ ሴቶች ቅድመ ምርመራ እንዲያደርጉ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የካንሰር ቅድመ ምርመራ እንዲደረግ እና በዚሁ እንዲቀጥል ታማሚዎች በራሳቸው የHPV ቴስት ናሙና ወስደው የሚመረመሩበትን መንገድ ለማመቻቸትና መንገድ ለመጥረግ የተቀረጸ ፕሮጀክት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎችን ብቃት ለማሳደግ ባለሙያዎቹ እና ሰልጣኞቹ ወደ አንድ ተቋም ሳይሄዱ በቨርቹዋል ፕላትፎርም እርስ በርስ የሚማሩበትን መንገድ አመቻችተናል ነው ያሉት።
በትዕግስት ግዛቸው