Fana: At a Speed of Life!

የአንድነት፣ የእርቅና የሰላም በዓል ”ያሆዴ”

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ”ያሆዴ” ተራርቀው የሚኖሩ በአንድ ላይ ተሰባስበው የሚያከብሩትና የተጣላ የሚታራቅበት፣ ቂም በቀል የሚተውበትና በብሔሩ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የአደባባይ በዓል ነው፡፡

”ያሆዴ” የመረዳዳትና የመተጋገዝ ዕሴት የሚጎላበት፤ የክረምት ጭጋግ አልፎ አሮጌውን ዓመት በመሸኘት አዲሱን ዓመት መቀበያ፤ የብሩህ ዘመን ተስፋ የሚሰንቅበት በዓል ነው፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሳሙኤል መንገሻ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ በዓሉን በድምቀት ለማክበር የዝግጅት ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

ያሆዴ ልዩ የሚያደርገው በሀገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩ የብሔሩ ተወላጆች እንዲሁም ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች በአንድ ላይ ሆነው የሚያከብሩት በዓል በመሆኑ ነው፡፡

በበዓሉ አከባበር ላይ የባህል ሽማግሌዎች ምርቃትን ጨምሮ የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች ይቀርባሉ፡፡

ይህ ታላቅ ባህላዊ ሀብት አዲሱን ዓመት በላቀ የሥራ ተነሳሽነት በልማትና በሰላም ለማሳለፍ የሚታቀድበት ጭምር ነው፡፡

ያሆዴ ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከችግርና ከማጣት ወደ ማግኘት የመሻገር በዓል ከመሆኑም በላይ፤ ከብሔሩ ባህላዊ እሴቶች መካከል አንዱ ነው፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች ለአዲሱ ዓመት የመልካም ምኞት የምርቃት ሥርዓት ያከናውናሉ፡፡

የአንድነት፣ የእርቅና የሰላም በዓል የሆነው ያሆዴ ሕዝቡ ቁርሾና ጥላቻን ከአሮጌው ዓመት ጋር ትቶ በአዲስ መንፈስና ራዕይ አዲሱን ዓመት የሚጀምርበት ነው፡፡

በዓሉ በፍቅር፣ በይቅርታና በመተሳሰብ የሚከበር በመሆኑ፤ ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም ግንባታ ከፍተኛ ፋይዳ አለው፡፡

ወጣቱ ትውልድ አባቶች ጠብቀው ያቆዩትን ይህንን ባህል ሳይበረዝ ለቀጣይ ትውልድ እንዲያስተላልፍ ባህሉን እንዲያውቅ ይደረጋል።

የሀዲያ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል በሆነው “ያሆዴ” የሚከወነው ጭፈራ ለበዓሉ ልዩ ድምቀት የሚያጎናጽፍ ማህበራዊ እሴት ነው።

የያሆዴ ጭፈራን ወጣት ወንዶች ተሰብስበው ለበዓሉ በየቤቱ እየተዘዋወሩ ምሽቱን ሙሉ ያዜማሉ፤ እንዲሁም ሴቶች በበዓሉ ላይ ጭፈራቸውን ያቀርባሉ፡፡

ይህንን ጭፈራ ልዩ የሚያደርገው ወጣቶች እየጨፈሩ ወላጆቻቸውንና ታላላቆቻቸውን የሚመርቁበት በመሆኑ ነው።በዕለቱ የሚከናወኑ ባህላዊ ክንዋኔዎች ሁሉ መልካም ምኞት፣ ሰርቶ የመለወጥና የመበልጸግ ተስፋ የሚሰነቅባቸው ናቸው፡፡

የዘንድሮው በዓል በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት፣ በወጣቶች ባህላዊ የያሆዴ ጭፈራ፣ በባህላዊ የምግብ አቀራረብ ሥነ ሥርዓት ታጅቦ በመጪው መስከረም 12 ቀን 2019 ዓ.ም በድምቀት ይከበራል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.