Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ምን አሉ?

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አሁን ሀሳብ መሬት ነክቷል። ራዕይ ተግባር ሆኗል።
ዛሬ በጂቡቲ ደመርጆግ የተካሄደው ተራ ሥነ ሥርዓት አይደለም። የአንድ አህጉር አዲስ ምዕራፍ መክፈቻ እንጂ። የአፍሪካ ቀንድ፣ ከግጭትና አለመግባባት ታሪኩ ወጥቶ፣ ወደ ትብብርና ወደ ጋራ ኢንቨስትመንት ዘመን ሲሸጋገር የሚያሳይ ምልክትም ነው።
አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ እውን ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ ይዛለች፡፡ ግዙፍ ራዕይ የምታልም ብቻ ሳትሆን፣ ያን ራዕይ መሬት ላይ የምታወርድ ሀገር መሆኗን በተግባር ያሳየችበት ሌላኛው ድሏ ነው፡፡
120 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ ቧንቧ መስመር፣ የጂቡቲዋን ደመርጆግ ወደብ ከምስራቅ ኢትዮጵያዋ ደወሌ ማከፋፈያ ጋር ያገናኛል። በ80 ሄክታር ስፋት ላይ የሚያርፈው ፕሮጀክቱ ÷ 375 ሺህ ኪዩቢክ ሜትር የማከማቻ አቅም ይኖረዋል፡፡
የ160 ሚሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት የሆነው ፕሮጀክቱ÷ የመተባበርና የመደመር ማሳያ ነው፡፡ አፍሪካውያን ለአፍሪካ ችግር መፍትሄ ሊፈጥሩ ተባብረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና የዳንጎቴ ግሩፕ፣ ሁለት አፍሪካዊ ካፒታሎች በአፍሪካ ምድር በጋራ አቅደው ተግብረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይሄንን የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ባኖሩበት ወቅት በ”የሎጂስቲክስ ወጭንና መዘግየትን በመቀነስ፣ የኢነርጂ ዋስትናን ያጠናክራል” ብለዋል።
ይህ ነጥብ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወሳኝ ትርጉም አለው። ኢትዮጵያ ባህር በር የሌላት እንደመሆኗ፣ ነዳጅ ከውጭ ስታስገባ፣ በእስካሁኑ ሥርዓት ላይ የትራንስፖርት መጨናነቅ፣ የመኪና ወረፋ፣ የመንገድ ላይ ጉዳት እና ተያያዥ ወጪዎች ያጋጥማሉ።
ነዳጅ በቧንቧ መስመር በቀጥታ ሲጓዝ ግን፣ እነዚህ ውጣ ውረዶች በእጅጉ ይቀንሳሉ፤ ጊዜም ገንዘብም ይድናል። ውጤቱ ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ የተረጋጋ ዋጋ፣ የተረጋገጠ አቅርቦት፣ የተጠናከረ የኢነርጂ ዋስትና በረከቶቹ ናቸው።
ትናንት፣ የኢትዮጵያና የጂቡቲ ግንኙነት በዋናነት የወደብ አገልግሎት ልውውጥ ነበር። ዛሬ ግን ወደ ላቀ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ ሁለቱም ሀገራት በጋራ ባለቤትነት፣ በጋራ ኢንቨስትመንት፣ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሰረተ ልማት እየገነቡ ነው።
ይህ ከደንበኛ አገልግሎት ሰጪ ግንኙነት ወደ እውነተኛ ኢኮኖሚያዊ አጋርነት የተደረገ ሽግግር ነው። ወደፊትም ይህ አጋርነት ወደ ሰፊ ቀጣናዊ ትስስር ሊያድግ የሚችልበት መሰረት ጥሏል።
ይህ ፕሮጀክት ከሁለቱ ሀገራት አልፎ ትልቅ ትምህርት ይዟል። ኢትዮጵያ ጂቡቲ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከቀላል የመተላለፊያ ስምምነት ወደ ጥልቅ የጋራ ኢንቨስትመንት አጋርነት እንዴት ማሸጋገር እንደሚችሉ ተምሳሌት ይሆናል።
ከዚህም በላይ፣ የአፍሪካውያን ገንዘብ በአፍሪካ መሰረተ ልማት ላይ ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ተጨባጭ ማረጋገጫ ይሰጣል፡፡ ይህ ደግሞ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ራዕይን ከወረቀት ወደ እውነታ የሚያሸጋግር ተግባራዊ ማሳያ ነው።
ይህ ቧንቧ መስመር ነዳጅ ብቻ አያስተላልፍም። በሁለት ህዝቦች መካከል የተዘረጋ የመተማመን ድልድይ ነው። ኢትዮጵያና ጂቡቲ ኢኮኖሚያዊ እጣ ፈንታቸውን በዚህ ትስስር በጋራ አዋህደዋል፡፡
ለአፍሪካ ቀንድ አዲስ የትብብር ምዕራፍ ነው። ለኢትዮጵያ ደግሞ ይህ ግንባታ ራሱ የሚናገረው ነገር አለ፡፡ ሀገሪቱ ራዕይ ብቻ የምትሰብክ ሳትሆን፣ ራዕይዋን መሬት ላይ የምታወርድ፣ ወደፊት የምትጓዝ ሀገር እንደሆነች ተጨማሪ ምስክርም ነው፡፡
በአፈወርቅ እያዩ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.