ስደተኛ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት ላይመለሱ ይችላሉ ሲል ተመድ ስጋቱን ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ስደተኛ ህፃናት በተለይም ሴቶች ወደ ትምህርት ቤት ላይመለሱ ይችላሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስጋቱን አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ በተለይም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ስደተኛ ህፃናት ወደ ትምህርት ቤት የመመለስ እድላቸውን አነስተኛ ያደርገዋል ሲል ነው ስጋቱን የገለፀው።
ከስደተኛ ህፃናት ግማሽ ያክሉ የኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ በነበሩ ጊዜያትም ትምህርት ቤት ያልገቡ መሆናቸውን ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
ሪፖርቱ በዓለም ላይ ከሚገኙ ስደተኞች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን የሚያስተናግዱ 12 ሀገሮችን መረጃ በመጠቀም ከ 1 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ወይም 48 በመቶ ለትምህርት የደረሱ ህጻናት እንደማይማሩ ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰው ተጽዕኖ በስደተኞች ይበልጥ የከፋ መሆኑን ያስታወቀው ተመድ፥ ህጻናትን በተለይም ሴቶችን ከትምህርት ውጭ ሊያደርግ እንደሚችል ነው ያመላከተው።
ምንጭ፦ አልጄዚራ