በቀይ ባህር ጉዳይ የሚደረጉ ውይይቶች የኢትዮጵያን ጥቅም ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፣ መስከረም 25፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በቀይ ባህር እና በቀጣናው የባህር በር ጉዳይ የሚደረጉ ውይይቶች የኢትዮጵያን ሕጋዊ ጥቅም ያገናዘቡ ሊሆኑ ይገባል አለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡
ሚኒስቴሩ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ከጠቅላላው የዓባይ ወንዝ (ብሉ ናይል) የውሃ መጠን ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነውን እንደምታበረክት አንስቷል፡፡
በዚህም ምክንያት በዓባይ ውኃ አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ የሚደረጉ ማናቸውም አይነት ውይይቶች ይህንን እውነት ከግምት ያስገቡ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝቧል፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የቀይ ባህርን የውሃ ክፍል በመልክዓ ምድርም በታሪክም የምትጋራ መሆኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫው አውስቷል፡፡
በታሪክ አጋጣሚዎች በሀገራት ፖለቲካዊ የወሰን መቀያየር ሁኔታዎች ቢከሰቱም፤ ኢትዮጵያ አሁንም ከቀይ ባህር በ30 ማይል ርቀት ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል፡፡
በዚህም ምክንያት በቀጣናው የደህንነትና የባህር በር ጉዳይ የሚደረጉ ውይይቶች የኢትዮጵያን ህጋዊ ጥቅምና ከቀይ ባህር ጋር ያላትን ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት ታሳቢ ማድረግ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
እነዚህ መልክዓ ምድራዊና ታሪካዊ እውነታዎች በፖለቲካዊ ትርክትና አግላይ ርምጃዎች እንዲሁም ቀጣናውን የማተራመስ እንቅስቃሴዎች ሊቀለበሱ አይችሉም ብሏል፡፡
የትኛውም የውክልና ጦርነትና የጸብ አጫሪ ድርጊት ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ህጋዊ ጥቅም፣ ሚና እና ኃላፊነት እንደማያስቀርና እና መሬት ላይ ያለውን እውነታ ሊቀይሩ እንደማይችል አስገንዝቧል፡፡
ኢትዮጵያ ሰላማዊ ግንኙነትን፣ የጋራ መከባበርና ቀጣናዊ ትብብርን መርህ ባደረገው አካሄዷ እንደምትቀጥል ያመለከተው መግለጫው ሀገሪቱ በሉዓላዊነቷ፣ በግዛት አንድነቷና መሰረታዊ ብሔራዊ ጥቅሞቿን እንደማትደራደር አረጋግጧል፡፡
በቀጣናው ያሉ ሀገራት ግጭትንና የዜሮ ድምር አካሄድን ከመከተል ይልቅ፤ ገንቢ በሆነ ውይይት፣ በአጋርነትና በመልካም ጉርብትና መርህ ላይ በመመስረት የጋራ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡