Fana: At a Speed of Life!

በሀገራዊ ምክክር ሒደት የቀረቡ ምክረ ሃሳቦችን ለመተግበር ይሰራል – ፕሬዚዳንት ታዬ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 26፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በሀገራዊ ምክክር ሒደት የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች እና የውይይት ውጤቶች ለዘላቂ ሀገር ግንባታ ያላቸው ፋይዳ እጅግ የላቀ ነው አሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፡፡

የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 7ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ ዓመት የጋራ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) ጨምሮ የሁለቱ ም/ቤቶች አባላት በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር÷ የጠብመንጃ ባሕልና የነፍጥ አዙሪትን በዘላቂነት ለማስቀረት በትኩረት እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የሀገራችን የተለምዶ የፖለቲካ ማጠንጠኛ ውስብስብ ከሆነው የአንባጓሮ፣ የአመጽና የግጭት ጎዳና በዘላቂነት ለመላቀቅ የፖለቲካ ልምምዳችን በሰላም፣ በንግግር፣ በዕውቀትና በመደማመጥ ላይ እንዲመሰረት መንግሥት በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል፡፡

በተለይ በሀገራዊ ምክክር ሒደት የቀረቡ ሃሳቦችና የውይይት ውጤቶች ለፖለቲካዊ ልምምዳችን እና ለዘላቂ ሀገር ግንባታ ያላቸው ፋይዳ እጅግ የላቀ ነው ሲሉ አውስተዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህ በውይይት የዳበሩ ሀገራዊ ሃሳቦች ወደ መሬት እንዲወርዱ የሚደረግ ይሆናል ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፡፡

ክዋኔያቸውም የኢትዮጵያን ፖለቲካ እና ማህበራዊ ንቃተ ሕሊና ከፍ የሚያደርጉ፣ የልዩነታችንን ክፍተት የሚያጠቡ እንዲሁም ሰላም የናኘባትና እድገት የነገሰባት ተምሳሌታዊ ሀገር የሚገነቡ ይሆናል ብለዋል፡፡

ሙስናን አምርሮ የሚጠየፍ ማሕበረሰብ፣ ሌብነትን የሚታገልና የሚያስወግድ ሥርዓት ለመዘርጋት የተጀመረውን ርምጃ መንግሥት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ድሎች የጠንካራ አፈጻጸም ማሳያ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

እነዚህን በውጤት የተገለጡ በጎ ልምዶችና ተሞክሮዎች በሁሉም አካባቢዎች በማስፋት ለቀጣይ ሀገራዊ እድገት አጉልተን እንጠቀማለን ሲሉም አረጋግጠዋል፡፡

#የመደመር_መንግሥት

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.