ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ለጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የእንኳን አደረሰዎት መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ለ25 ዓመታት በማገልገል የብር ኢዮቤልዩአቸውን እያከበሩ ላሉት የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ የእንኳን አደረሰዎት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ናሬንድራ ሞዲ እአአ ከ2001 እስከ 2014 የጉጃራት ግዛት ዋና ሚኒስትር፣ ከዚያ ወዲህ ደግሞ የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ እና ህንድ አጋርነት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሁለገብ አጋርነት እና ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸውም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ህንድ ኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ እንድትቀላቀል ያደረገችው ድጋፍ ጠቅሰው፤ በአዲስ አበባ ለህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ያደረጉትን አቀባበል አስታውሰዋል፡፡
በቅርቡ ለብሪክስ ጉባኤ ወደ ህንድ ያደረጉትን የመጀመሪያ ጉብኝት ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህንን አጋርነት ይበልጥ እንደሚያጠናክሩም ገልጸዋል፡፡